በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በዓለም ዙሪያ 110 ሚሊዮን ሰዎች እንደተፈናቀሉ ተመድ አስታወቀ


በዓለም ዙሪያ 110 ሚሊዮን ሰዎች እንደተፈናቀሉ ተመድ አስታወቀ
please wait

No media source currently available

0:00 0:01:52 0:00

በዓለም ዙሪያ፣ 110 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች፣ ከመኖሪያቸው በኃይል መፈናቀላቸውን፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል። በዚኽ መጠን ሰዎች ከመኖሪያቸው ሲፈናቀሉ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደኾነም ተጠቁሟል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ፣ ከትላንት በስቲያ ሰኞ፣ በጀኒቫ ለዜና ሰዎች እንዳሉት፣ በፈረንጆቹ 2022 መጨረሻ፣ 108ነጥብ4 ሚሊዮን የሚኾኑ ሰዎች፣ በጦርነት እና በሰብአዊ መብቶች ጥሰት ምክንያት ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል። ይህም፣ ከቀደመው ዓመት ጋራ ሲነጻጸር፣ በ19 ሚሊዮን ጭማሪ አሳይቷል።

ሩሲያ፣ በዩክሬን ላይ በፈጸመችው ወረራ ምክንያት ጭማሬው መታየቱን፣ ግራንዲ ጨምረው ገልጸዋል። ቁጥሩ፣ ከ108ነጥብ4 ሚሊዮን ወደ 110 ሚሊዮን ያደገውም፣ ባለፉት ስምንት ሳምንታት፣ በሱዳን በመካሔድ ላይ ያለው ግጭት፣ ወደ ሁለት ሚሊዮን ሰዎችን በማፈናቀሉ ነው፤ ብለዋል።

“እንደምታስታውሱት፣ ከሁለት ዓመታት በፊት፣ ምናልባትም ባለፈው ዓመት፣ የተፈናቃዮች ቁጥር ከ100 ሚሊዮን ማለፉን አስታውቀን ነበር። አሁን፣ 10 በመቶ ጭማሬ አሳይቷል። ዓለም ያለበትን አስከፊ ኹኔታ የሚያሳይ ነው፤” ብለዋል ግራንዲ፣ ጀኒቫ ላይ ሲናገሩ።

ፊሊፖ ግራንዲ ይፋ ያደረጉት አኀዝ፣ በስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽኑ በየዓመቱ የሚወጣው፣ በመላው ዓለም የሚገኙ የተፈናቃዮች ኹኔታ ሪፖርት አካል ነው።

ከተፈናቃዮቹ ውስጥ፣ 35 ሚሊዮን የሚኾኑት፣ ድንበር ተሻግረው እና አገራቸውን ለቀው ለመውጣት ሲገደዱ፣ 62 ሚሊዮን የሚኾኑት ደግሞ፣ በአገር ውስጥ የተፈናቀሉ ናቸው። ግራንዲ በተጨማሪም፣ ዜግነታቸው ያልተወሰነ ወይም ዜግነታቸውን የወሰዱበት አገር የማይታወቅ ሰዎች ቁጥር፣ 4ነጥብ4 ሚሊዮን መድረሱን ተናግረዋል።

ዝቅተኛ ወይም መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሀገራት፣ ከባለጸጋ ሀገራት በበለጠ፣ ተፈናቃዮችን በማስተናገድ ላይ እንደኾኑም ታውቋል። ተፈናቃዮችን ተቀብለው በሚያስተናግዱ ሀገራት ላይ፣ አሉታዊ ተጽእኖው እየጨመረ እንደኾነ የጠቆሙት ግራንዲ፣ 27 የሚኾኑ የአውሮፓ ኅብረት አባል ሀገራት፣ ስደተኞችንና ፍልሰተኞችን በተመለከተ ሓላፊነትን ለመጋራት፣ ባለፈው ሳምንት መወሰናቸውን በመልካም እንደሚቀበሉት አስታውቀዋል።

XS
SM
MD
LG