በህክምና ምክንያት ከእስራት የተለቀቁት የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ጄከብ ዙማ ወደወህኒ ቤት እንዲመለሱ ከፍተኛው የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ውሳኔ ሰጠ።
ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት እአአ ባለፈው ዐመት ችሎት በመዳፈር በቀረበባቸው ክስ ታስረው የነበሩት ዙማ እንዲለቀቁ ያደረገው ውሳኔ ህገ ወጥ ነው ማለቱን ሊንዳ ጊቭታሽ ከጆሐንስበርግ ዘግባለች።
ጂከብ ዙማ በህመም ምክንያት ከእስር ያስፈታቸው የከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ እንዲጸና ያቀረቡት የይግባኝ አቤቱታ ዛሬ ሰኞ ውድቅ ተደርጎባቸዋል።
የሰማኒያ ዓመቱ ዙማ እአአ 2021 ሀምሌ ወር ውስጥ ነበር ችሎት በመዳፈር ወንጀል የአንድ ዓመት ከሦስት ወር የእስራቅ ቅጣት የተበየነባቸው። ቅጣቱ የተወሰነባቸውም በእርሳቸው የሥልጣን ዘመን በመንግሥት ባለሥልጣናት ስለተፈጸሙ የሙስና አድራጎቶች ለብሄራዊ መርማሪ አካል ቃላቸውን እንዲሰጡ የተላከላቸውን መጥሪያ አክብረው ባለመቅረባቸው መሆኑ ይታወሳል።
ይህንኑ ተከትሎ በተለይም በሳቸው የትውልድ ክፍለ ግዛት በኳዙሉ ናታል እና የሀገሪቱ የኢኮኖሚ መናሃሪያ በሆነችው በጋዉቴንግ በደጋፊዎቻቸው የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ተቀጣጥሎ በስፋት ሁከት እና ዝርፊያ ተፈጽሟል።
ዙማ ሁለት ወር ላልሞላ ጊዜ ከታሰሩ በሁዋላ ህመማቸው ምን እንደሆን ሳይገለጽ በህመም ምክንያት ከወህኒ ቤት እንዲወጡ ተደረገ። ዙማን ያስፈታቸውን ውሳኔ ባለፈው ታህሳስ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ቀለበሰው። ሆኖም የኋለኛውን የፍርድ ቤት ውሳኔ በመቃወም የቀረበው ሙግት ለረጅም ጊዜ በመቀጠሉ ዙማ እስከዛሬዋ ዕለት ድረስ ወህኒ ቤት ሳይመለሱ ቆይተዋል።
ዙማን "አግባብ በሌለው ምክንያት ከእስር እንዲፈቱ ያደረገው ውሳኔ ህግን የተላለፈ ነው" የሚለውን የከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ እንዲጸና ነው ዛሬ የይግባኝ አቤቱታዎች ሰሚው ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ያጸናው።
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ከወህኒ ቤት ውጪ ያሳለፉት ጊዜ ሊቆጠርላቸው አይገባም የሚለውን የከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሳኔ ግን የይግባኝ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ አላጸናውም። ቢያጸናው ኖሮ ዙማ የተሰጣቸውን የአስራ አምስት ወራት እስራት ቅጣት ሙሉ በሙሉ ታስረው ማጠናቀቅ ይጠበቅባቸውነበር።
ያን የሀገሪቱ የህግ ታራሚዎች አገልግሎት ኮሚሽኑ እንዲወስንበት መርቶታል።
የዙማ ፓርቲ ገዢው የአፍሪካ ብሄራዊ ኮንግሬስ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በዛሬው የፍርድ ቤት ውሳኔ ላይ አስተያየት አልሰጠም።
ተቃዋሚው የዲሞክራሲያዊ ህብረት ፓርቲ በበኩሉ "ዙማም እንደማናቸውም የሀገሪቱ ዜጋ የእስራት ቅጣታቸውን እንዲፈጽሙ ኮሚሽኑ የከፍተኛ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተግባራዊ ማድረግ አለበት" ሲል ጥሪ አቅርቧል።
ዙማ ጉዳያቸውን ከመጀመሪያው ችሎት በመዳፈር ወንጀል የጥፋተኝነት ውሳኔ ወደሰጣቸው ወደህገ መንግሥታዊው ፍርድ ቤት ወስደው ሊከራከሩ ይችላሉ።