ዩናይትድ ስቴትስ ሚኔሶታ ክፍለ ግዛት ውስጥ በግል ንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩት ኢትዮጵያዊ አሜሪካዊ አቶ ተሺታ ቱፋ ባለፈው አርብ አዲስ አበባ ቦሌ አውሮፕላን ጣቢያ በቁጥጥር ስር ውለው ትናንት መለቀቃቸውን ቤተሰቦቻቸው ለቪኦኤ ገለጹ። አቶ ተሺታ “ሜትሮፖሊታን ትራንስፖርቴሽን ኔትወርክ” የተባለ ኩባኒያ ፕሬዚዳንት እና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው።
የባለሃብቱን እስርና መለቀቅን በተመለከተ ለአሜሪካ ድምፅ ማብራሪያ የሰጡት ወንድማቸው አቶ ትቤሶ ቱፋ፤ አቶ ተሺታ እናታቸውን ለማስታመም ከርሳቸው ቀደም ብለው ወደኢትዮጵያ ተጉዘው እንደነበረ ገልጸው ሁለቱም አርብ ዕለት ወዩናይትድ ስቴትስ ለመመለስ ቦሌ አውሮፕላን ጣቢያ ከገቡ በኋላ አቶ ተሺታ መወሰዳቸውን ገልጸዋል።
ወንድማቸው በምን ምክንያት እንደታሰሩ እንደማያውቁ የተናገሩት አቶ ትቤሶ “ተለቀዋል” የሚለውን ዜና በተመለከተ "እኛ መፈታቱን የምናረጋግጠው ዩናይትድ ስቴትስ ምድር ሲገባ ነው"የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ቪኦኤ ስለአቶ ተሺታ ቱፋ ጉዳይ ከኢትዮጲያ መንግሥት ባለሥልጣናት እና ከአዲስ አበባ የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።
የአፋን ኦሮሞ ባልደረባችን ትዕግሥት ገሜ ያጠናቀረችውን ዘገባ ቆንጅት ታየ ታቀርበዋለች።