በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ያቆመውን ርዳታ ከወር በኋላ ሊቀጥል እንደሚችል አስታወቀ


የዓለም ምግብ ፕሮግራም ያቆመውን ርዳታ ከወር በኋላ ሊቀጥል እንደሚችል አስታወቀ
please wait

No media source currently available

0:00 0:01:59 0:00

የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ በኢትዮጵያ አቋርጦት የነበረውን የምግብ ሥርጭት፣ በመጪው ወር ሊቀጥል እንደሚችል ተስፋ አለው፤ ሲሉ፣ አንድ የፕሮግራሙ ከፍተኛ ባለሥልጣን፣ ትላንት ሰኞ አስታውቀዋል።

የፕሮግራሙ ከፍተኛ ባለሥልጣን እንዳሉት፣ ትክክለኛውን የርዳታ ተደራሽ በመሳቱ የተቋረጠው የምግብ ዕደላ ሊቀጥል የሚችለው፣ ምግቡ በቀጥታ ለማን ይደርሳል በሚለው ላይ፣ ፕሮግራሙ የበለጠ ቁጥጥር እና ውሳኔ ሰጪ ከኾነ ነው።

ወደ አገር ውስጥ ለርዳታ የሚገባው ምግብ ይሰረቃል፤ በሚል፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ ባለፈው ግንቦት፣ ለትግራይ ክልል የሚሰጠውን ርዳታ አቋርጦ ነበር። በዚኽ ወር ደግሞ፣ በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን ርዳታ ማቋረጡ ይታወሳል።

ፕሮግራሙ፥ ከሁለቱም ውሳኔዎች ላይ የደረሰው፣ በኢትዮጵያ መንግሥት ውስጥ ባሉ ሰዎች እና መዋቅሮች ጭምር የተደገፈ የርዳታ ምግብ ዘረፋ ተፈጽሟል፤ በሚል፣ የአሜሪካ መንግሥት ርዳታውን ማቋረጡን ተከትሎ ነው።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም(WFP) ይኹን የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ልማት ድርጅት(USAID)፣ በስርቆቱ ቀጥተኛ ተጠቃሚ ማን እንደነበር አልገልጹም፤ ሲል የሮይተርስ ዘገባ አመልክቶ፣ ለውጭ የተራድኦ ድርጅቶች በውስጥ በተሠራጨ መረጃ ግን፣ የተወሰነ ምግብ፥ ለኢትዮጵያ ሠራዊት እንደተሰጠ ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ የተሰረቀ ምግብ መቀበሉን አስተባብሏል። መንግሥት በበኩሉ፣ በጉዳዩ ላይ ምርመራ እያደረገ እንደኾነ ገልጾ፣ የምግብ ርዳታው መቋረጡ፣ ሰብአዊ ቀውሱን ያባብሰዋል፤ በሚል ወቀሳውን አቅርቧል።

በኢትዮጵያ፣ ከ20 ሚሊዮን በላይ ሰዎች፣ የምግብ ርዳታን ይሻሉ። ችግሩ የከፋውም፣ ለረጅም ጊዜ በዘለቀው ድርቅ እና ለሁለት ዓመታት በተካሔደው ጦርነት ምክንያት ነው።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ የፕሮግራም እና የፖሊሲ ረዳት ሥራ አስፈጻሚ ቫለሪ ጓርኔሪ እንደሚሉት፣ በትግራይ እና በስደተኞች መጠለያ ላሉ ሰዎች፣ ርዳታው በፈረንጆቹ አቆጣጠር በመጪው ሐምሌ አጋማሽ ሊጀምር እንደሚችል ጠቁመዋል።

ባለሥልጣኗ አክለው እንዳሉት ግን፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ የአካባቢ እና የክልል ባለሥልጣናት፣ ምግቡን ማን እንደሚቀበል በመወሰን ረገድ ያላቸውን ሚና መቀነስ ይፈልጋል። “እኛ ራሳችን በቀጥታ ውሳኔ ውስጥ ለመግባት እንፈልጋለን፤” ሲሉ ተደምጠዋል ሓላፊዋ።

ጓርኔሪ በተጨማሪም፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ውሳኔ እና አሠራር ትክክል እንደነበር ተከራክረዋል። ርዳታው፣ ለታሰበላቸው ሰዎች መድረሱን ለማረጋገጥ፣ “ድንገተኛ ውሳኔ ለመወሰንና የአሠራር ለውጥ ለማድረግ ተገደናል፤” ብለዋል ሓላፊዋ።

XS
SM
MD
LG