በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኢትዮጵያ መስፋፋቱ ተረስቷል የተባለው ኤች.አይ.ቪ በዐዲስ መልክ ከፍተኛ ሥርጭት እያሳየ ነው


በኢትዮጵያ መስፋፋቱ ተረስቷል የተባለው ኤች.አይ.ቪ በዐዲስ መልክ ከፍተኛ ሥርጭት እያሳየ ነው
please wait

No media source currently available

0:00 0:06:47 0:00

· ቫይረሱን ለመዋጋት አሜሪካ የተጨማሪ 112 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ መመደቧን አስታውቋለች

ኤች.አይ.ቪ፣ በኢትዮጵያ፣ በዐዲስ መልክ እየተሠራጨ እንደኾነ፣ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

የሰሜን ኢትዮጵያውን ጨምሮ፣ በአገሪቱ የተከሠቱ ግጭቶች፣ በኤች.አይ.ቪ መከላከል እና መቆጣጠር እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ጫና እንዳሳደረ የጠቀሰው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ፣ በአገሪቱ፣ በዓመት 11ሺሕ ሰዎች እንደሚሞቱና 8ሺሕ300 ሰዎች በቫይረሱ እንደሚያዙ ገልጿል።

ቫይረሱ በፍጥነት እየተሠራጨ ካሉባቸው አከባቢዎች መካከል፥ የጋምቤላ፣ የዐማራ ክልል እና የዐዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተጠቃሽ እንደኾኑና ምክንያቱም መዘናጋት እና ትኩረት ማጣቱ ነው፤ ተብሏል።

አሜሪካ፣ በኢትዮጵያ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስን ለመቆጣጠር የሚያስችል፣ ተጨማሪ 112 ሚሊዮን ዶላር መመደቧን፣ ትላንት አስታውቃለች።

ዐዲሱ የአሜሪካ ድጋፍ፣ በተለይ በወጣቶች ዘንድ፣ በፍጥነት እየተዛመተ ያለውን ኤችአይ.ቪን፣ ለመከላከል እና ለመቆጣጠር አንደሚያግዝ፣ ሚኒስቴር መሥራያ ቤቱ አመልክቷል።

በጤና ሚኒስቴር የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ጽሕፈት ቤት ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፈቃዱ ያደታ፣ ኤች.አይ.ቪ በኢትዮጵያ፣ በዐዲስ መልክ በመሠራጨት ላይ እንደኾነ አስታውቀዋል።

ቫይረሱ ጋራ እንደሞኖሩ በግልጽ በመናገር፣ ስለ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ላለፉት 19 ዓመታት በማስተማር የሚታወቁት ወይዘሮ ዘነበች ቲሮሬ፣ ቫይረሱ፥ በዐዲስ መልክ እየተሠራጨ ያለበትን ምክንያት ሲያስረዱ፣ ከዓመታት በፊት የነበረውንና የአሁኑን በማነጻጸር፣ “ችግሩ በሽታውን መርሳት ነው፤” ብለዋል።

የትግራይ ክልልን መነሻ አድርጎ በሰሜን ኢትዮጵያ የተካሔደውን ጦርነት ጨምሮ በአገሪቱ የተከሠቱ ግጭቶች፣ የኤች.አይ.ቪን መስፋፋት በመከላከል እና በመቆጣጠር እንቅስቃሴ ላይ፣ ከፍተኛ ጫና ማሳደራቸውንም ገልጸዋል።

በዐማራ ክልል ብቻ፣ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መድኃኒት ሲወስዱ የነበሩ 65ሺሕ ሰዎች፣ በጦርነቱ የተነሣ መድኃኒታቸውን አቋርጠው እንደነበረ፣ አቶ ፈቃዱ ተናግረዋል።

በአገሪቱ በዓመት 11ሺሕ ሰዎች በበሽታው እንደሚሞቱና ዐዲስ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ደግሞ፣ 8ሺሕ300 እንደሚደርሱ፣ ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ አስታውቋል።

በቫይረሱ በዐዲስ መልክ እየተያዙ ካሉት ዜጎች 70 መቶዎቹ ወጣቶች ሲኾኑ፣ ከ15 እስከ 24 በኾነው የዕድሜ ክልል እንደሚገኙም ተናግረዋል።

ቫይረሱ በፍጥነት እየተሠራጨ ካሉባቸው አካባቢዎች መካከል፣ የጋምቤላ እና የዐማራ ክልሎች እና የዐዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተጠቃሽ ናቸው፤ ያሉት አቶ ፈቃዱ፣ መዘናጋት እና ትኩረት ማጣቱ፣ ለከፍተኛ መስፋፋቱ አስተዋፅኦ ማድረጉን አስረድተዋል፡፡

የጋምቤላ ክልል ጤና ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ወንድማገኘሁ በላይነህ፣ በክልሉ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ሥርጭት እየጨመረ የመጣው፣ ከአካባቢ ኹኔታ እና ከግንዛቤ ማነስ ጋራ በተገናኙ መንሥኤዎች እንደኾነ፣ በስልክ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

ቢሮው፣ በ2016 ዓ.ም. ትኩረት አድርጎ ከሚሠራባቸው ጉዳዮች ውስጥ፣ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስን ሥርጭት መከላከል እና መቆጣጠር አንዱ መኾኑን ዲሬክተሩ አመልክተዋል።

በሌላ በኩል በትግራይ ክልል፣ በጦርነቱ ምክንያት በተፈጠረው ክፍተት፣ የቫይረሱ መዛመት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ስለመኾኑ ምልክቶች መኖራቸውን፣ የክልሉ ጤና ቢሮ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከያ እና መቆጣጠርያ አስተባባሪ ከዚህ ቀደም ለአሜሪካ ድምፅ ገልፆ ነበር።

አስተባባሪው አቶ ፍሥሓ ብርሃነ፣ ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ማብራርያ፥ ከጦርነቱ በፊት የፀረ-ኤች.አይ.ቪ መድኃኒት ተጠቃሚ ከነበሩ ከ46 ሺሕ በላይ ሰዎች መካከል 13 ሺሕ የሚኾኑቱ፣ የት እንዳሉ እንደማያውቁም ተናግረው ነበር።

ቫይረሱ አሁንም በኢትዮጵያ በፍጥነት በመሠራጨት ላይ መኾኑን ከመርሳት ባሻገር፣ የኮንዶም እጥረት መኖሩ ሌላው ምክንያት እንደኾነ፤ ወይዘሮ ዘነበች ይናገራሉ።

አሜሪካ፣ በኢትዮጵያ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስን መስፋፋት ለመግታት ብሎም ቫይረሱን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የሚያስችል፣ ተጨማሪ 112 ሚሊዮን ዶላር መመደቧን፣ ሰሞኑን አስታውቃለች።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ፣ በአገሪቱ በሚገኙ ከ11ሺሕ በላይ ወረዳዎች፣ እንደ ሥርጭት ደረጃቸው በሦስት በመክፈል፣ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ በአሜሪካ የተመደበው ዐዲሱ በጀት፣ በተለይ በወጣቶች ዘንድ የቫይረሱን በፍጥነት መዛመት ለመከላከል እና ለመቆጣጠር እንደሚያግዝ፣ አቶ ፈቃዱ ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡

የጽ/ቤቱ ሥራ አስፈጻሚ አያይዘውም፣ ይኸው ድጋፍ፣ በግጭት የተጎዱ አካባቢዎችን ጨምሮ፣ በመላ አገሪቱ የቫይረሱን መስፋፋት ለመቆጣጠር የሚደረጉ ጥረቶች እና የሚሰጡ አገልግሎቶች እንዲጠናከሩ ያስችላል፤ ብለዋል።

በተለየ ኹኔታም፣ ለቫይረሱ ተጋላጭ በኾኑ ዜጎች ማለትም ሴተኛ አዳሪዎች፣ አደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚዎች እና የረጅም ርቀት ሹፌሮች ላይ ያተኮረ ሥራ እንደሚከናወንም ጠቁመዋል።

አሜሪካ፣ ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2030፣ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስን ለመቆጣጠር የያዘችውን ዕቅድ ለማሳካት የሚያስችል፣ ተጨማሪ 112 ሚሊዮን ዶላር(ከስድስት ቢሊዮን ብር በላይ) ለመለገስ ቃል ገብታለች።

በኢትዮጵያ፣ ባለፉት 20 ዓመታት፣ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር፣ ሦስት ቢሊዮን ዶላር የድጋፍ በጀት ፈሰስ ማድረጓን፣ በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ፣ ለቪኦኤ የላከው መረጃ ያመለክታል።

በኢትዮጵያ አሁን ወቅት፣ ከ610 ሺሕ በላይ ዜጎች ከቫይረሱ ጋራ እንደሚኖሩ፣ ከ500 ሺሕ በላይ የሚኾኑቱ ደግሞ ከቫይረሱ ጋራ እንደሚኖሩ አውቀው መድኃኒት በመውሰድ ላይ እንዳሉ ተገልጿል።

XS
SM
MD
LG