በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

“በህወሓት ስም ፓርቲ አታቋቁሙም” የተባሉ ግለሰቦች ፍርድ ቤት እንደሚሔዱ ገለጹ


“በህወሓት ስም ፓርቲ አታቋቁሙም” የተባሉ ግለሰቦች ፍርድ ቤት እንደሚሔዱ ገለጹ
please wait

No media source currently available

0:00 0:06:16 0:00

‘ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ’/‘ህወሓት’/ በሚል መጠሪያ፣ ዐዲስ ፓርቲ ለመመሥረት ጥያቄ አቅርበው ውድቅ የተደረገባቸው ግለሰቦች፣ ለፍርድ ቤት ይግባኝ እንደሚሉ ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ከትላንት በስቲያ ሰኞ፣ ሰኔ 5 ቀን 2015 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው ደብዳቤ፣ ‘ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ’/‘ህወሓት’/ በሚል መጠሪያ ዐዲስ ክልላዊ ፓርቲ ለማቋቋም የቀረበ የቅድመ ዕውቅና ፈቃድ ጥያቄን ውድቅ ማድረጉን አስታውቋል::

ቦርዱ፥ ‘ህወሓት’ በሚል ስም፣ የዐዲስ ፓርቲ መቋቋምን የማይቀበለው፣ ከዚኽ ቀደም፥ መሠረቱን በትግራይ ክልል አድርጎ በሌሎች የኢትዮጵያ አከባቢዎችም ሲንቀሳቀስ የነበረ በመኾኑ፣ በመራጮች ዘንድ ግርታን ሊፈጥር ይችላል፤ በማለት እንደኾነ ገልጿል፡፡

አቶ ገብረ ሚካኤል ተስፋይ በተባሉ የአደረጃጀት ኮሚቴ ሰብሳቢነት እና ሌሎች ሦስት ሰዎች አወያይነት፣ ግንቦት 12 ቀን 2015 ዓ.ም. በተደረገ ስብሰባ፣ ‘ህወሓት’ በሚል መጠሪያ፣ ክልላዊ ፓርቲ ለመመሥረት በመወሰን፣ ግንቦት 21 ቀን 2015 ዓ.ም. በ120 መሥራች አባላት ፊርማ የተደገፈ የቅድመ እውቅና ጥያቄ፣ ለምርጫ ቦርድ ቀርቦ እንደ ነበር፣ ቦርዱ ይፋ ያደረገው ደብዳቤ ያስረዳል።

በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና በምርጫ ሥነ ምግባር ዐዋጅ ቁጥር 1162/2011 መሠረት፣ የቀረበለትን የጊዜያዊ ፈቃድ ጥያቄ፣ አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋራ አነጻጽሮ

መመርመሩን የገለጸው ቦርዱ፣ በዚኽ ስም፣ ዐዲስ ፓርቲ ቢቋቋም፣ መራጮችን የሚያደናግር በመኾኑ፣ የቀረበለትን የቅድመ ዕውቅና ፈቃድ ጥያቄ እንዳልተቀበለው አስታውቋል።

‘ህወሓት’/ በሚል ስም ፓርቲ ለማቋቋም፣ ለቦርዱ ጥያቄ ካቀረቡ ግለሰቦች አንዱ፣ አቶ ይሥሓቅ ወልዳይ፥ የምርጫ ቦርድን ውሳኔ በመቃወም፣ በይግባኝ ወደ ፍርድ ቤት እንደሚወስዱት አመልክተዋል::

አቶ ይሥሓቅ እና ሌሎቹ በህወሓት ስም ዐዲስ ፓርቲ ለማቋቋም ጥያቄ ያቀረቡት ግለሰቦች፣ ቀደም ሲል፣ “ፈንቅል” በሚል ስም፣ ህወሓትን ተቃውመው የወጣቶች እንቅስቃሴ ሲያካሒዱና ሲመሩ የነበሩ ናቸው፡፡ ህወሓትን ስትቃወሙ እንዳልነበራችኹ ሁሉ፣ በህወሓት ስም ዐዲስ ፓርቲ ማቋቋም የወሰናችኹት ለምንድን ነው? የሚል ጥያቄ ያቀረብንላቸው አቶ ይሥሓቅ፣ “የወይንነት መጠሪያ የያዘው ህወሓት፥ የትግራይ ሕዝብ ታሪክ ስለኾነ ወደ ሕዝቡ ለመመለስ ነው፤” ብለዋል፡፡

አቶ ይሥሓቅ አክለውም፣ በአሁኑ ጊዜ፣ በትግራይ ክልል መኖሩ የሚታወቀው ህወሓት፣ በምርጫ ቦርድ ሕጋዊነት እንደሌለውና ይህን ክፍተት ታሳቢ በማድረግ፣ የቅድመ ዕውቅና ፈቃድ ጥያቄውን እንዳቀረቡ ገልፀው፤ ታሪካዊ ያሉትን ህወሓትን እንደ ፓርቲ ለመውረስ እንደሚሹም፣ አቶ ይሥሓቅ ተናግረዋል፡፡

የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ(ህ.ወ.ሓ.ት) ሊቀ መንበር ዶክተር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል፣ ፓርቲው የተሰረዘ ሕጋዊ ህልውናውን ለማስመለስ፣ እንደ ዐዲስ የዕውቅና ማመልከቻ ማስገባት እንደሚኖርበት፣ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተላለፈውን ውሳኔ እንደማይቀበሉት፣ ለቦርዱ በሰጡት ምላሽ ገልጸው ነበር፡፡

50 ዓመት ዕድሜ ያለውን ሰው፣ እንደ ዐዲስ አኹን ጀምር እንደማለት ነው፤” በሚል ያነጻጸሩት ሊቀ መንበሩ፣ “ረዥም ዕድሜ ያለው ፓርቲ ራሱ፣ በሌላ መንገድ ካልፈረሰ በቀር ይቀጥላል፤” ብለዋል። ጉዳዩን ለአፍሪካ ኅብረትም ማሳወቃቸውን ተናግረው ነበር፡፡

የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት፣ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ከተጀመረ ከኹለት ወር ተኩል በኋላ፣ ህወሓት ኃይልን መሠረት ያደረገ የዐመፃ ተግባር ላይ መሳተፉን እንዳረጋገጠ ጠቅሶ፣ የፓርቲው ሕጋዊ ሰውነት እንዲሰረዝ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ጥር 10 ቀን 2013 ዓ.ም. ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ በዚኹ ውሳኔውም፥ የፓርቲው ሓላፊዎች፣ በፓርቲው ስም እንዳይንቀሳቀሱ፣ የፓርቲው ንብረት ህወሓት ዕዳ ካለበት እንዲከፍል እና ቀሪው ንብረት ለሥነ ዜጋ እና ለመራጮች ትምህርት እንዲውልም አዝዟል፡፡

ህወሓት፣ ሚያዝያ 28 ቀን 2015 ዓ.ም. ለቦርዱ በጻፈው ደብዳቤ፣ በትግራይ ክልል የነበረው ጦርነት፣ በሰላማዊ እና ሕገ መንግሥታዊ መንገድ እንዲፈታ፣ ፓርቲው ከፌደራሉ መንግሥት ጋራ ስምምነት ላይ መድረሱን ጠቅሶ፣ የቦርዱ የቀደመ ውሳኔ እንዲነሣለት መጠየቁን፣ ቦርዱ ባለፈው ወር ገልጿል፡፡

ቦርዱም፣ ግንቦት 4 ቀን 2015 ዓ.ም. ባካሔደው ስብሰባ፣ የፓርቲውን ጥያቄ መመርመሩንና የቀደመ ውሳኔው፣ ዐዋጅን መሠረት አድርጎ የተላለፈ መኾኑን አውስቶ፣ “ምንም እንኳን በደብዳቤው ላይ እንደተገለጸው፣ ለቦርዱ ውሳኔ መነሻ የኾነው፣ ኃይልን መሠረት ያደረገ የዐመፃ ተግባር፣ አሁን ባይኖርም፣ ሕጋዊ ሰውነቱን ዳግም ለፓርቲው ለመመለስ የሚያስችሉ ድንጋጌዎች፣ በዐዋጅ ቁጥር 1162/2011 ላይ ተደንግገው ስለማይገኙ፣ ጥያቄውን ውድቅ አድርጎታል፡፡

በወቅቱ ህወሓት፣ የቦርዱ ውሳኔ፥ የፕሪቶርያውያን የሰላም ስምምነት እና ሕግን መሠረት ያላደረገ በመኾኑ፣ በሕግም በፖለቲካም ተቀባይነት የለውም፤ በሚል ተቃውሞታል፡፡ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደርም በበኩሉ፣ የህወሓት ድርጅታዊ ህልውና በሕግ የተሰረዘበት የቦርዱ

ውሳኔ፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩን ጠቅላላ ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል፣ እንዲሁም የሰላም ስምምነቱን የሚፈታተን ነው፤ በማለት መቃወሙ ይታወሳል፡፡

በተያያዘ ለአራት ተከታታይ ቀናት የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ማካሄዱን ጠቅሶ መግለጫ ያወጣው ህወሓት፤ ፓርቲው ለማፍረስ ተቀናጅቷል ያለውን ሴራ በጥበብ እንደሚታገለው ገልጿል።

ህወሓት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያቀረበው የሕጋዊ ሰውነት ስረዛ ጥያቄ ውድቅ መደረጉ፤ የሰላም ስምምነቱን የሚጥስና ቅንነት የጎደለው ቴክኒካዊ ስህተት መሆኑን የገለፀው ህወሓት ፤ ይህንን ለማስተካከል የተጀመረ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ እንዳለ ጠቁሟል።

/ሙሉ ዘገባውን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ይከታተሉ/

XS
SM
MD
LG