በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሀገራዊ ምክክር ተሳታፊዎች ልየታ እና አጀንዳ ማሰባሰብ በቀጣዮቹ ወራት እንደሚጠናቀቅ ተገለጸ


የሀገራዊ ምክክር ተሳታፊዎች ልየታ እና አጀንዳ ማሰባሰብ በቀጣዮቹ ወራት እንደሚጠናቀቅ ተገለጸ
please wait

No media source currently available

0:00 0:17:21 0:00

የኹሉን አቀፍ ሀገራዊ ምክክር ተሳታፊዎችን ልየታ እና አጀንዳ የማሰባሰብ ሥራን፣ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ ታቅዷል፡፡

በቀጣዩ ዓመትም፣ በማያግባቡ ዋና ዋና አጀንዳዎች ላይ ሀገራዊ ምክክር ለማስጀመር እንደታቀደ፣ ኮሚሽኑ ለአሜሪካ ድምፅ ገልጿል፡፡

በአምስት ክልሎች እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር፣ የተሳታፊዎች ልየታ እና አጀንዳ የማሰባሰብ ሒደቱ እየተገባደደ እንደኾነ የገለጹት፣ የኹሉን አቀፍ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርኣያ፣ ቀሪ ክልሎችንና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በማሳተፍ ሥራው በአጭር ጊዜ እንደሚከናወን አመልክተዋል፡፡

በምክክሩ ላይ ተስፋ አለማድረግ፣ ከቆየው የጥርጣሬ ባህላችን የሚመነጭ ነው፤ የሚሉት ፕሮፌሰር መስፍን፣ ውጤታማ ለመኾን ከዚኽ ዐይነቱ እሳቤ መውጣት እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ፡፡

መሠረታዊ የልዩነት እና የግጭት መንሥኤ በኾኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ፣ በሕዝቦች መካከል ምክክር በማድረግ መግባባት እንዲፈጠር የማስቻል ተልዕኮ አንግቦ፣ በዐዋጅ ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባ አንድ ዓመት ከአምስት ወራት ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ በአሁኑ ወቅት፣ በተለያዩ ክልሎች እየተዘዋወረ የምክክሩን ተሳታፊዎች የመለየት እና አጀንዳዎችን የማሰባሰብ ሥራ በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርኣያ፣ ከአሜሪካ ድምፅ ጋራ በነበራቸው ቆይታ፣ ካለፈው ግንቦት ወር ጀምሮ፣ በአምስት ክልሎች እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር፣ የተሳታፊዎች ልየታ እና የአጀንዳ አሰባሰብ ሒደቱ እየተከናወነ እንደኾነ አስረድተዋል፡፡

ከሕዝብ ባሰባሰብነው ምክረ ሐሳብ መሠረት፣ የልየታ እና አጀንዳ የማሰባሰብ ሥራው፥ ጾታ፣ የሥራ ዘርፍ፣ ዕድሜ እና መሰል ልዩነቶችን ታሳቢ በማድረግ፣ ዘጠኝ ባለድርሻ አካላትን ያካተተ፣ ከየወረዳው ከ450 እስከ 500 ሰዎችን በመጥራት እየተከናወነ ይገኛል፡፡ ተሳታፊዎችን ከወረዳ በመመልመል ሒደት ላይ ደግሞ ከሲቪክ ማኅበራት፣ ከዕድሮች እና መሰል ዘርፎች የተውጣጡ፣ ከየወረዳው ሰባት ተባባሪ አካላት እንደሚረዷቸው፣ ፕሮፌሰር መስፍን ተናግረዋል፡፡

በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና የተለያዩ የክልል እና የፌዴራል መንግሥት አካላትም፣ የምክክር አጀንዳዎችን እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም፣ የምክክር አጀንዳ አለኝ የሚል ማንኛውም ግለሰብ፣ አጀንዳውን ማቅረብ እንደሚችል አስታውቀዋል፡፡

ለዚኹ ዓላማ፣ በኮሚሽኑ ዋና መሥሪያ ቤት፣ ሣጥን ተዘጋጅቶ እንደተቀመጠም ተመልክተናል፡፡ በአጠቃላይ፣ የተሳታፊዎች ልየታ እና አጀንዳ የማሰባሰብ ሒደቱ፣ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ተገባዶ፣ በሚቀጥለው ዓመት ምክክሩ እንደሚጀመር፣ ዋና ኮሚሽነሩ አመልክተዋል፡፡

ኬኔዲ አባተ ከፕሮፌሰር መስፍን አርኣያ ጋራ ያደረገውን ቆይታ ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።

XS
SM
MD
LG