በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የማርከስ ሳሙኤልስን “ባልትና በተርታ ማእድ በገበታ”


የማርከስ ሳሙኤልስን “ባልትና በተርታ ማእድ በገበታ”
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:11 0:00

· ስለ ባህላዊ ምግብ አዘጋጆች የፖድካስት ስርጭት ጀመረ

ታዋቂው ትውልደ ኢትዮጵያዊ ባለሞያ ማርከስ ሳሙኤልሰን፣ ከታወቀበት የምግብ ዝግጅት በተጨማሪ፥ ሴቶች፣ ጥቁሮች እና ነጭ ያልኾኑ የባህላዊ ምግብ ቤት ባለቤቶችንና መሥራቾችን ለማስተዋወቅ እና ለማበረታት፣ "A Seat at the Table" የተሰኘ ፖድካስት ማዘጋጀቱን አሶሴይትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡

የምግብ ባለሞያው ማርከስ ሳሙኤልሰን፣ ስለሚያሰነዳቸው ልዩ ልዩ ምግቦች ብቻ ሳይኾን፣ ዝነኛ ለኾነው ምግብ ቤቱ ስለሚቀጥራቸው ሠራተኞቹም በእጅጉ የሚጨነቅ እንደ ኾነ ይናገራል፡፡

“እኔ በጣም ለማደግ የምጣጣር ነኝ፤” ያለው ሳሙኤልሰን፣ “ምናልባትም የተወለድኹት በደሳሳ ጎጆ፣ አመጣጤም ከአነስተኛ ቤተሰብ ስለኾነ ይኾናል፡፡ ኾኖም፣ እጅግ በጣም አድርጌ አመሰግናለኹ፡፡ ምግብ ቤቶቼ የምንኖርበት ማኅበረሰብ ነጸብራቅ መኾናቸውም አይደል፤ ስለዚኽ፣ በሃቭ ኤንድ ማር ምግብ ቤታችን፣ የጥቁሮች አመራር እና የሴቶች አመራር እንዲኖር ወስነናል፤ ምክንያቱም በዚያ ረገድ ክፍተት ነበር፤” ብሏል፡፡

የሳሙኤልሰን፣ ሬድ ሮስተር የተከፈተው ሃርለም ውስጥ ሲኾን፣ “በኢንዱስትሪያችን ውስጥ ለጥቁሮች እና ጠያይም ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠር እንፈልጋለን፤” በማለት ስፍራውን የመረጠበትን ምክንያት ያስረዳል፡፡ አያይዞም፣ “ምግብ ማዘጋጀትን በጣም ስለምወድ፣ ያ ዕድል ለኹሉም ሰው እኩል እንዲዳደረስ እፈልጋለኹ፤ ዕድሉ ፍትሐዊ ኾኖ ለኹሉም እኩል መዳረስ ይኖርበታል፤” ሲል ያለውን ትልም አብራርቷል፡፡

በሴቶች እና ነጭ ባልኾኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች የተከፈቱ ምግብ ቤቶችን ክብር ለመስጠት እና ለማበረታታት፣ በሳሙኤልሰንና ተከታዩ ሼፍ ጆናታን ዋክስማን፣ “ኤ ሲት አት ዘ ቴብል” የተባለ ስምንት ክፍሎች ያሉት በድምፅ የተዘጋጀ ተከታታይ የፖድካስት ፕሮግራም ባላፈው ዓመት አስቀድሞ መሰናዳቱን ዘገባው አመልክቷል፡፡

በፖድካስት ትረካው ውስጥ፣ የምግብ ባለሞያ ሼፎች እንዲሁም፣ ብዙ ምግብ ቤቶች ሲቋቋሙ አንሥቶ ተሳትፎ የነበራቸው፥ አሜሪካ ውስጥ እጅግ ልዩ እና ታዋቂ የነበሩትና በአልበርት ራይት የተጀመሩት እንደ ኒውዮርኩ ፈር ቀዳጅ ጄዘቤል፤ በዓሊ ቤተሰብ በዋሽንግተን ዲሲ የተቋቋመው ቤንስ ቺሊ ቦውል እንዲሁም በቻርለስ ፋን ሳንፍራንሲስኮ ውስጥ የተከፈተው ዘስላንትድ ዶር የተሰኘው ምግብ ቤቶች ይገኙበታል፡፡

ምግብ፣ የፖድካስቱ ትኩረት ኾኖ ያገለግላል፡፡ ልዩ ልዩ ተቋሞች፥ በማኅበረሰቦች እና ባህሎች ላይ፣ የቁርስ እና የሳንድዊች ሥጋ እና ድንች በመሳሰሉት አማካይነት ተጽእኖ በማሳደር ማገልገላቸው ተገልጿል፡፡

“የጥቁሮች ታሪኮቻችን አንድ ነጠላ ነገር ብቻ አለመኾናቸውን እናውቃለን፤” የሚለው ሳሙኤልሰን፣ “የጥቁሮች ታሪክ ከሚዘክርበት ወር ወደ ሴቶች ታሪካዊ ወር ስንሸጋገር፣ ይህን ነገር ማጋራት በጣም አስፈላጊ መሆኑ ተሰምቶኛል፤” በማለት አግባብነቱን ያስረዳል፡፡

በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የተወለደው ሳሙኤልሰን፣ ወላጅ እናቱ፣ እ.ኤ.አ. በ1970 በሳንባ ነቀርሳ ከሞተችበት በኋላ፣ ወደ ስዊድን በጉዲፈቻ ተወስዶ ማደጉን የሕይወት ታሪኩ ያስረዳል፡፡ ወደ ሬስቶራንት በሚገባበት ጊዜ ኹሉ፣ “ወደ አሜሪካ ታሪክ በቅንጭቡ እንደገባኹ ያህል ይሰማኛል፤” የሚለው ሳሙኤልሰን፣ “ኤ ሲት አት ዘ ቴብል በሚለው ፕሮግራማችን መያዝ የምንፈልገው ነገር እርሱን ነው፤” በማለት ዓላማውን አስገንዝቧል፡፡ አክሎም፣ “ከምግቡም ባሻገር ነገርዬውን የተለየ የሚያደርጉት ሰዎች ናቸው፤” ሲልም ብሏል፡፡

“A Seat at the Table” በሚል በድምፅ የተተረከው የማርከስ ሳሙኤልሰን የፖድካስት ፕሮግራም፣ መደመጥ መጀመሩን አሶሴይትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡ ታዋቂው የምግብ ዝግጅት ባለሞያ፣ “ባልትና በተርታ ማእድ በገበታ” እያለን ይኾን?

XS
SM
MD
LG