በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኤም-ኖማድ የቴክኖሎጂ ኩባንያ በኬንያ የከብት ግብይቱን በማሳለጥ እያገዘ ነው


ኤም-ኖማድ የቴክኖሎጂ ኩባንያ በኬንያ የከብት ግብይቱን በማሳለጥ እያገዘ ነው
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:03 0:00

የዋጋ አለመረጋጋት፣ የተጠቃሚዎች ዝቅተኛ የመግዛት ዐቅም፣ እንዲሁም ከብት አርቢዎች ያላቸው የገበያ አማራጭ ውስንነት፣ ለዓመታት፣ የኬንያን የቁም ከብት ገበያ ሲገዳደር የከረሙ ማነቆዎች ናቸው።

ኤም-ኖማድ የተሰኘውና በናይሮቢ የሚገኘው ወጣኒ የቴክኖሎጂ ኩባንያ፣ በገጠር ያሉ ከብት አርቢዎች፣ የመረጃ መረብን በመጠቀም ከብቶቻቸውን እንዲሸጡ መድረክ ከፍቶላቸዋል። በሰሜን ምሥራቅ ኬንያ በሚገኘውና ዋጂር በተሰኘው ከተማ ባለው የቁም ከብት ገበያ፣ ኢብራሂም አሕመድ በማለዳ እየመጣ ከብት አርቢዎቹን፣ ኤም- ኖማድ የተሰኘውንና በኢንተርኔት ከብቶቻቸውን መሸጥ የሚችሉበትን መድረክ ሲያስተዋውቃቸው ይውላል።

ኢብራሂም አሕመድ፣ ገጸ ድሩን የከፈተው፣ አብድራህማን አሕመድ ከሚባል ሌላ ግለሰብ ጋራ በመኾን፣ ከአራት ዓመታት በፊት ነበር። እርሱ እንደሚለው፣ በገጠር ያሉ አነሰተኛ ከብት አርቢዎች፣ ከብቶቻቸውን ለመሸጥም ኾነ ከሌላ ለመግዛት፣ ቀላል መንገድ ተከፍቶላቸዋል። “እንዲህ ዐይነቱ ገበያ መጥተን፣ ከብት አርቢዎችን እንመዘግባለን። ያላቸውን የከብት ብዛት እና ዋጋ የመሳሰሉትን መረጃዎችን እንሰበስባለን። ከዚያም፣ በጅምላ ከብት ከሚገዙትና ወደ እነዚኽ ገበያዎች መምጣት ከማይችሉ ገዢዎች ጋራ እናገናቸዋለን፤” ሲል ተደምጧል ኢብራሂም፡፡

ኢብራሂም አሕመድ እንደሚለው፣ ኤም-ኖማድ የተሰኘው ድረ ገጽ፣ ሻጭንና ገዢን በማገናኘት፣ እስከ ሞቃዲሹ ርቀው ለሚገኙ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ደንበኞች፣ ግብይት እንዲፈጽሙ አስችሏል። “የኤም-ኖማድ አንዱ ጠቀሜታ፥ ለከብት አርቢዎቹ የተሻለ ዋጋ ያስገኝላቸዋል። የቁም ከብት ገበያው ከሚሰጣቸው፣ ከ20 እስከ 25 በመቶ የተሻለ ዋጋ እናስገኝላቸዋለን፤” ሲል አክሏል ኢብራሂም።

ኤም-ኖማድ፣ ገልጂር የተሰኘው ኩባንያ፣ የመጀመሪያ ሥራው ነው። በሰሜን ኬንያ፣ 10 የገበያ ሥፍራዎችን ይሸፍናል። ከ300 በላይ ከብት አርቢዎችን መዝግቦ ይዟል። ሲያድ ዓሊ፣ ከእነዚኽ አንዱ ነው።

“እኔ ከብት አርቢ ስኾን፣ 78 ፍየሎች አሉኝ። ከብቶቼን፣ ርቀው ለሚገኙ ገዢዎች በመሸጥ ትርፍ አግኝቻለኹ። ለወደፊቱም፣ ብዙ መሸጥ ነው የምፈልገው፤” ብሏል ሲያድ።

የኬንያ የግብርና ሚኒስቴር እንደሚገምተው፣ በአገሪቱ 60 በመቶ የሚኾነው የከብት ሀብት የሚገኘው፣ በደረቃማ እና ከፊል ደረቃማ በኾኑ አካባቢዎች ነው። በእነዚኽ አካባቢዎች ለሚኖሩ አብዛኞዎቹ ሰዎች፣ ከብቶቻቸው ዋና የገቢ ምንጭ ናቸው። ባለሥልጣናት ደግሞ በአንጻሩ፣ የእንስሳት ርባታ ዘርፉ በማሽቆልቆል ላይ ነው፤ ይላሉ።

“አምስት የዝናብ ወቅቶች በድርቅ(ቦና ኾነው) አልፈዋል። 30 በመቶ የሚኾኑትን ከብቶቻችንን አጥተናል። ከችግሩ ለመውጣት፣ የመመገቢያ ቦታዎችን፣ የከብቶች ማደለቢያዎችንና የመኖ ማምረቻዎችን፣ ከአጋሮቻችን ጋራ ኾነን በሙከራ ደረጃ እያቋቋምን ነው፤” ብለዋል፣ በዋጂር አውራጃ፣ የእንስሳት ርባታ ሓላፊው ጉዋድ ጉልዬ።

በኬንያ፣ የእንስሳት ርባታ ዘርፉ ያልተማከለ ነው። የዘርፉ ሞያተኞች እንደሚሉት፣ አውራጃዎች፣ ገንዘብ እየመደቡ የገበያውን ኹኔታ ሥርዐት ማሲያዝ አለባቸው። “መንግሥት፣ ከብቶቻችንን ለውጭ አገር ገበያ እንድናቀርብ እንዲያግዘን እንሻለን፤ ምክንያቱም፣ አሁን ገበያው መጥፎ ነው። ከሞቃዲሹ እና ከናይሮቢ ውጪ፣ ሌላ ገበያ የለንም። ርዳታ እንሻለን፤” ሲሉ ተናግረዋል፣ በዋጂር የእንስሳት ገበያ ሊቀ መንበር የኾኑት ሙሳ ማሊም።

በያዝነው የፈርንጆች ዓመት መጨረሻ፣ ኤም-ኖማድ፥ ሥራውን ወደ ቀረው የኬንያ ክፍል ብሎም ወደ ጎረቤት ሀገራት ለማዳረስ ዐቅዷል።

XS
SM
MD
LG