በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በ2016 በጀት ረቂቅ ዐዲስ የካፒታል ፕሮጀክቶች እና የሠራተኞች ቅጥር አለማካተቱ ምክር ቤቱን አወያየ


በ2016 በጀት ረቂቅ ዐዲስ የካፒታል ፕሮጀክቶች እና የሠራተኞች ቅጥር አለማካተቱ ምክር ቤቱን አወያየ
please wait

No media source currently available

0:00 0:06:42 0:00

ዐዲስ ፕሮጀክቶችንና የሠራተኞች ቅጥርን እንደማያካትት የተገለጸው፣ የ2016 ዓመት በጀት ረቂቅ፣ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በርካታ ጥያቄዎችን አሥነስቷል፡፡

ካለፈው ዓመት ጋራ ሲነጻጸር፣ የ1ነጥብ9 በመቶ ብቻ ብልጫ ያለው፣ የ2016 ዓመት በጀት ረቂቅ፣ የተጀመሩ የልማት ፕሮጄክቶችን ታሳቢ በማድረግ እና የዋጋ ግሽበትን መቀነስ በሚያስችል መልኩ መዘጋጀቱን፣ የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሺዴ ገልጸዋል፡፡

የተወካዮች ምክር ቤት፣ በበጀት ረቂቁ ላይ በተወያየበት ወቅት፣ መንግሥት፥ ባለፈው ዓመት ከውጭ አጋሮች የበጀት ድጎማ እንዳላገኘ ያወሱት ሚኒስትሩ፣ በ2016 ዓ.ም. ይኖራል ተብሎ ከታቀደው ገቢ እና ርዳታ፣ 7ነጥብ9 የሚኾነው፣ ከልማት አጋሮች ይገኛል ተብሎ እንደታቀደ አመልክተዋል፡፡

ካለው የበጀት ውስንነት ጋራ በተያያዘ፣ እንደ ዘንድሮው ሁሉ፣ በዐዲሱ የበጀት ዓመት ረቂቅም፣ ዐዲስ የካፒታል ፕሮጀክቶች እና የሠራተኞች ቅጥር እንደማይኖርም አስታውቀዋል፡፡ የምክር ቤቱ አባላትም፣ የተለያዩ ጥያቄዎችን አንሥተው ውይይት ተደርጎበታል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሺዴ፣ ትላንት፣ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ተወስኖ ወደ ፓርላማው የተመራውን፣ የ801ነጥብ65 ቢሊዮን ብር በጀት ረቂቅ ዝርዝር፣ ዛሬ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበዋል፡፡ በአጠቃላይ፣ ከተያዘው የበጀት ረቂቅ ውስጥ፣ ከታክስ እና ታክስ ያልኾኑ ምንጮች፣ እንዲሁም ከውጭ ርዳታ፣ 520ነጥብ6 ቢሊዮን ብር ለማግኘት እንደታቀደ፣ ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡

በ2015 ዓ.ም. የበጀት ዓመት፣ ከውጭ አጋሮች ይገኛል ተብሎ የታቀደው የበጀት ድጎማ፣ ሙሉ በሙሉ እንዳልተገኘ ያስታወሱት ሚኒስትሩ፣ ለ2016 በጀት ዓመት፣ 41ነጥብ1 ቢሊዮን ብር ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል፡፡

ለ2016 ዓ.ም. የበጀት ዓመት የተያዘው አጠቃላይ የበጀት መጠን፣ ካለፈው ዓመት ጋራ ሲነጻጸር፣ የ1ነጥብ9 በመቶ ብቻ ብልጫ ያመለከቱት አቶ አሕመድ ሺዴ፣ ይህም በዋናነት፣ በጀቱ አገራዊ ዐቅምን፣ እንዲሁም የዋጋ ግሽበትን መከላከልን ታሳቢ አድርጎ እንደተዘጋጀ አብራርተዋል፡፡ ከዚኽ ጋራ በተያያዘ፣ በጀቱ፥ ለሚፈለጉ የልማት ሥራዎች በቂ ባለመኾኑ፣ ዐዲስ ፕሮጀክቶች እንደማይጀመሩ፣ እንዲሁም የዐዲስ መንግሥታዊ ሠራተኞች ቅጥርም እንደማይፈጸም አስታውቀዋል፡፡

ማብራሪያውን ተከትሎ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላቱ፣ ልዩ ልዩ ጥያቄዎችን አንሥተው የገንዘብ ሚኒስትሩ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ከውጭ አጋሮች የሚገኘው ርዳታ እንዲጨምር፣ መንግሥት እያከናወነ ስላለው የዲፕሎማሲ ሥራ የተጠየቁት አቶ አሕመድ ሺዴ፣ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የበጀቱ ረቂቅ ታሳቢ ከአደረጋቸው ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ በጦርነት የወደሙ

ንብረቶችንና የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን መልሶ የመገንባት፣ እንዲሁም ተጎጂዎችን መልሶ የማቋቋም እንደሚገኝበትና ከቀጣዩ በጀት ዓመት 20 ቢሊዮን ዶላር፣ ለዚኹ ተግባር እንደተያዘ፣ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

ለመልሶ ግንባታ እና ማቋቋም ሥራው፥ የአምስት ዓመት ፕሮጀክት ተቀርጾ፣ ከውጭ አጋሮች ጋራ በትብብር እየተሠራ እንደኾነ አስረድተዋል፡፡ በዚኹ ጉዳይ ላይ፣ ከጥቂት ቀናት በኋላ፣ ከአጋሮቹ ጋራ ውይይት እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡

ዛሬ ከቀትር በኋላ፣ በ2016 በጀት ረቂቅ ላይ ውይይት ያደረገው፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለዝርዝር እይታ፣ ለፕላን በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል፡፡

XS
SM
MD
LG