በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ተጋኗል የተባለው የዐዲስ አበባ የመሬት ሊዝ ጨረታ ዋጋ


ተጋኗል የተባለው የዐዲስ አበባ የመሬት ሊዝ ጨረታ ዋጋ
please wait

No media source currently available

0:00 0:09:18 0:00

- “ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የለውም፤ ለዜጎች ስጋት ሆኗል” - ባለሞያ

ከአምስት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በወጣው የመሬት ሊዝ ጨረታ፣ በአንድ ካሬ ከብር 20 ሺሕ እስከ ብር 414 ሺሕ እንደተሸጠ፣ የከተማ አስተዳደሩ የመሬት ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ይፋ አድርጓል፡፡

የባንክ ባለሞያውና የቀድሞ ፖለቲከኛ ሙሼ ሰሙ፣ በጨረታው የታየው የተጋነነ ዋጋ፣ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት እንደሌለውና ሒደቱ፥ በሽያጭ እና ግዥ አቅርቦት መካከል ያለውን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት እንደሚያዛባው አስረድተዋል፡፡ በአንጻሩ መንግሥት፣ ከጊዜያዊ ይልቅ ዘለቄታዊ ጥቅምን በሚያመጡ ጉዳዮች ላይ ሊያተኩር እንደሚገባ መክረዋል።

በሌላ በኩል፣ በጨረታው፥ በአንድ ካሬ እስከ 695 ሺሕ ብር ድረስ ዋጋ ቀርቦ እንደነበር፣ የዐዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማት እና አስተዳደር ቢሮ የለማ መሬት ማስተላለፍ እና ሊዝ ክትትል ሓላፊ አቶ ተስፋዬ ጥላሁን ገልጸዋል፡ በዚህም አስተዳደሩ፣ በአንዴ መክፈል ለሚችሉ ቅድሚያ በመስጠት፣ 414 ሺሕ ብር ያቀረቡ እንዲያሸንፉ ማድረጉን አስታውቀዋል።

የዐዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ከአምስት ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ፣ ግንቦት 9 ቀን 2015 ዓ.ም. የመሬት ሊዝ ጨረታ ማስታወቂያ አውጥቷል፡፡ በጨረታው፣ አጠቃላይ ስፋታቸው 143 ሺሕ ካሬ ሜትር ወይም 14ነጥብ3 ሄክታር የሆኑ 298 ቦታዎችን በሊዝ አቅርቦ ነበር፡፡

ለጨረታ የቀረቡት ይዞታዎች መነሻ ዋጋ፣ ከፍተኛው 2ሺሕ213 ብር እንደኾነ፣ የከተማ አስተዳደሩ የመሬት ልማት አስተዳደር ቢሮ መረጃ ያሳያል፡፡ ከሰሞኑ ይፋ በተደረገው የጨረታ ውጤት፣ ከተጫረቱት ቦታዎች መካከል፣ በአራዳ ክፍለ ከተማ፥ ለአንድ ካሬ ሜትር ቦታ 414 ሺሕ ብር ከፍተኛ የሊዝ ዋጋ እንደቀረበ፣ የከተማ አስተዳደሩ አስታወቋል፡፡ ይህም፣ በኢትዮጵያ የሊዝ ጨረታ ከፍተኛው ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ በከፍተኛ ኹኔታ ጨረታውን ያሽነፉት ግለሰብ፣ ለ410 ካሬ ባዶ ቦታ፣ ብር 169 ሚሊዮን 740 ይከፍላሉ።

ዮናስ ይመኑ፣ የጨረታውን ሰነድ ገዝቶ ለመሳተፍ ቢፈልግም፣ በነበረው ሰልፍ ምክንያት፣ ሳይሳካለት እንደቀረ ይናገራል፡፡ በከተማው በንግድ ሥራ የሚተዳደረው ዮናስ፣ የጨረታ ውጤቱ ከወጣ በኋላ የታየው ከፍተኛ ዋጋ እና የከተማ አስተዳደሩ

ከሊዝ ጨረታ ጋራ በተገናኘ ያወጣቸው ዐዲስ ሕጎች፣ እንደ እርሱ በጉጉት ሲጠበቁ የነበሩ ሰዎችን ተስፋ እንዳስቆረጣቸው ይገልጻል፡፡

በኢትዮጵያ ፖለቲካ በነበራቸው ተሳትፎና በማኅበራዊ የትስስር ገጻቸው ወቅታዊ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ሁኔታዎችን በተመለከተ በሚያጋሯቸዉ ጽሐፎች፣ የሚታወቁት ከፍተኛ የባንክ ባለሞያው አቶ ሙሼ ሰሙ፣ መንግሥት፣ ለረጅም ጊዜ የመሬት አቅርቦትን ዐቅቦ በመቆየቱ፣ ፍላጎቱን ከፍተኛ እንዳደረገው ይገልጻሉ፡ ይህ ደግሞ እጥረቱን አባብሶ፣ የመሬት ዋጋ እንዲንር እንዳደረገው ያስረዳሉ፡፡ ይኹንና፣ አሁን በመሬት ሊዝ ጨረታው የታየው የተጋነነ ዋጋ፣ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት እንደሌለው፣ ይናገራሉ፡፡

የከተማ አስተዳደሩ የመሬት ልማት አስተዳደር ቢሮ፣ በተካሔደው የመጀመሪያ ዙር የመሬት ሊዝ ጨረታ፣ በአጠቃላይ 297 ያህል ቦታዎችን ለጨረታ አቅርቧል፡፡ አራት ቦታዎች፣ ለጨረታ ብቁ ባለመኾናቸው፣ እንዲሁም ሌሎች ስድስት ቦታዎች ደግሞ በቂ ተጫራቾች ባለማግኘታቸው ሰርዟቸዋል፡፡ የቀሩት 13 ሄክታር ገደማ ስፋት ባላቸው 287 ቦታዎች ላይ ባካሔደው ጨረታ፣ 12ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ገቢ እንዳገኘ ገልጿል፡፡

በጉዳዩ ላይ፣ የአሜሪካ ድምፅ ያናገራቸው፣ የዐዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማት እና አስተዳደር ቢሮ የለማ መሬት ማስተላለፍ እና ሊዝ ክትትል ሓላፊ አቶ ተስፋዬ ጥላሁን፣ የመሬት ሊዝ ጨረታው ውጤት፥ ታዛቢዎች እና ተሳታፊዎች ባሉበት ይፋ እንደተደረገ ገልጸዋል።

በጨረታው፣ በካሬ እስከ 695ሺሕ ድረስ ዋጋ ቀርቦ እንደነበረ፣ ሓላፊው አንሥተዋል፡፡ የከተማ አስተዳደሩም፣ ክፍያውን በአንድ ጊዜ መክፈል ለቻሉ ቅድሚያ በመስጠት፣ 414 ሺሕ ብር ያቀረቡ ተወዳዳሪ እንዲያሸንፉ ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡ ይህም፣ የቀረበው የሊዝ ጨረታ ዋጋ፣ በነጻ ገበያ የመጣ እንጂ፣ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ ገንዘብ ለመሰብሰብ በሚል አለመተመኑን እንደሚያረጋግጥ በመጥቀስ፣ ከዋጋው መናር ጋራ በተያያዘ የሚሰነዘረው ወቀሳ፣ ተገቢነት እንደሌለው ተናግረዋል፡፡

በመንግሥት፣ የመሬት ሊዝ ጨረታዎች ላይ፣ ገዥዎች የሚያቀርቧቸው የተጋነኑ ዋጋዎች፣ ሌሎች ግለሰቦችም በተመሳሳይ ሽያጮች ላይ ዋጋ እንዲጨምሩ በመገፋፋት፣ በሽያጭ እና ግዥ አቅርቦት መካከል ያለውን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት እንደሚያዛባ አቶ ሙሼ ሰሙ ያስረዳሉ፡፡

የተጋነኑ ዋጋዎች የሚያሳድሩትን ስጋት ለመቅረፍ፣ መንግሥት፥ ከጊዜያዊ ይልቅ ዘለቄታዊ ጥቅሞችን በሚያመጡ ጉዳዮች ላይ ሊያተኩር እንደሚገባ፣ አቶ ሙሼ ሰሙ ይመክራሉ።

በጨረታው፣ ከፍተኛ ገንዘብ በማቅረብ ያሽነፉ ግለሰቦችን የገንዘብ ምንጭ ሕጋዊነትን ለማጣራት፣ ሙከራ እንደተደረገ፣ ሓላፊው አቶ ተስፋዬ ጥላሁን ገልጸዋል።

የመሬት ሊዝ ጨረታ ሰነዱን ለማግኘት ያልተሳካለቸ አቶ ዮናስ ይመኑ፣ አሁን ያለው ሁኔታ ግን በየጊዜው እየተጋነነ የመጣው የቤት እና የመሬት ዋጋ መናር፣ “መኖሪያ አልባ እንዳልሆን፤” ከሚለው ስጋታቸው ጋራ እንዲኖሩ እንደፈረደባቸው ገልፀውልናል።

ላለፉት አምስት ዓመታት፣ የሊዝ ጨረታ ተቋርጦ የቆየው፣ ከመሬት ጋራ የተያያዙ የሕግ፣ የተደራሽነት እና ፍትሐዊነት ችግሮችን ለማስተካከል ጊዜ በመውሰዱ መሆኑን የጠቀሱት ሓላፊው አቶ ተስፋዬ፤ ከዚኽ በኋላም፣ በዓመት ሁለት ጊዜ የሚወጣበትን ኹኔታ ለማመቻቸት እየተሠራ እንደኾነ አመልክተዋል፡፡ ስለ ጨረታ ሰነድ ሽያጭ አሠራር የሚነሡ ቅሬታዎችን ለመፍታትም፣ በቴክኖሎጅ የታገዘ እንዲኾን ጥረት እንደሚደረግ፣ ሓላፊው አስታውቀዋል፡፡

XS
SM
MD
LG