በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ከአፍሪካ ወደ ውጭ አገር የሚሸሸው ገንዘብ ከውጭ እርዳታ ከእጥፍ በላይ ይበልጣል


ችግሩ በአፍሪካ ከተደቀኑ የኢኮኖሚ ችግሮች ከቀዳሚዎቹ መሆኑን አንድ ጥናት ጠቁሟል

ህገ-ወጥ የገንዘብ ፍሰት በጠቅላላው የአንድን አገር ድንበር አቋርጦ ህገ-ወጥ በሆኑ መንገዶች የተገኙ ገንዘቦች የሚዘዋወሩበት መንገድ ነው። በሙስና፡ በኮንትሮባንድ፣ በወንጀል ድርጊትና ቀረጥ ላለመክፈል የሚዛወር ሂሳብ ነው።

ስሌቱና ቁጥጥሩ በጣም የተወሳሰበ በመሆኑ ለባለሙያዎቹም ቢሆን እራስ ምታት የሆነ ችግር ነው። ቁጥሩ ግን ለማንኛውም ሰው የሚገባና እራስን የሚያስይዝ ነው።

ወደ አፍሪካ አህጉር እስከዛሬ ድረስ በእርዳታ መልኩ ከተለገሰው ገንዘብ ጋር ሲነጻጸር ከአፍሪካ የሚወጣው ህገ-ወጥ ገንዘብ በእጥፍ፣ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ደግሞ እስከ ሶስት እጥፍ ይበልጣል።

ሬይመንድ ቤከር Global Financial Integrity የተባለ ድርጅትን ይመራሉ። አንድ ሰው በህይወቱ ሊያየው ከሚገባ በላይ ከአፍሪካ ገንዘብ በህገ-ወጥ መልኩ ሲወጣ ተመልክቻለሁ፤ በጥናትም አስደግፌ አረጋግጫለሁ ይላሉ። ሁኔታው አስደንጋጭ ነው ይላሉ።

“በጣም ብዙ ነው። ከአፍሪካ በህገ-ወጥ መልኩ የሚወጣው ገንዘብ የአህጉሪቱን ኢኮኖሚ በስፋት የሚጎዳ ነው። ለትምህርት፣ ጤናና ሌሎች ለማህበራዊ አገልግሎቶች የሚውለውን ገንዘብ ያሟጥጣል። የአገሬው ባለሃብቶች በልማት ላይ የሚያደርጉትን የገንዘብ ፍሰጥ ይቀንሳል፤ ብድር እንደልም ማግኘትን ያግዳል፣ የኑሮ ውድነትን ያስከትላል፣ የውጭ ምንዛሬ እጦትን ያባብሳል…ብዙ ብዙ ችግሮች አሉት። በጥናታችን እንደጠቆምንው ድሃ አገሮችን በእጅጉ እየጎዱ ካሉ የኢኮኖሚ ሁኔታዎች ትልቅ ድርሻ ያለው እክል ነው።”

በዚህ እክል እንደ አፍሪካ ክፉኛ የተጎዳ የአለም ክፍል የለም። በአለም ዙሪያ ከታዳጊ አገሮች የሚወጣው ህገ-ወጥ የገንዘብ ፍሰት በአመት 1 ትሪሊየን ዶላር ይሆናል። ይህንን ሁኔታ በቁጥር ለማስቀመጥ ግሎባል ፋይናንሻል ኢንተግሪቲ ሁለት ለረጅም ጊዜ በግልጋሎት ላይ የነበሩ ቀመሮችን ይጠቀማል። የአለም ባንኩ residual method እና የአለም የገንዘብ ድርጅት IMF Direction of Trade Statistics.

ሳይንሱን ለተመራማሪዎቹ እንተወውና፤ ለሁላችንም በሚገባ መልኩ ከቀመሮቹ የተገኙት ውጤቶች ላይ እናተኩል።

በህገ-ወጥ መልኩ ገንዘብ የሚወጣባቸው መንገዶች በሙስና፡ በኮንትሮባንድ፣ በወንጀል ድርጊት (ማለት በአደንዛዥ እጽ ዝውውርና) ቀረጥ ላለመክፈል የሚዛወር ሂሳብ ናቸው።

በተለምዶ የአፍሪካ ሀብት ከሀገር ይዛወራል የሚባለው፤ ለረጅም ጊዜ አገር በሚመሩ አምባ-ገነኖችና አጋሮቻቸው እንደሆነ ይነገራል። ይሄ መንገድ በእርግጥ ብዙ የአገር ሀብት የሚወጣበት ቢሆንም እንደ ሬይመንግ ቤከር አባባል ያለው ድርሻ በጣም ጥቂት ነው።

“ድንበር ተሻግሮ በሚደረግ የህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ከጉቦና ከስርቆት የሚገኘው ገንዘብ 3ከመቶ የሚሆነውን አለም አቀፍ ዝውውር ብቻ ነው የሚወስደው። ከወንጀል የሚገኘው፤ ማለት ከአደንዛዥ እጽ ንግድ ከወሮበላነትና ከመሳሰሉት የሚገኘው ወደ 33-35 ከመቶ የሚሆነውን ነው የሚሸፍነው” ይላሉ ቤከር።

ከ60-65 ከመቶ የሚሆነውን የአለም አቀፍ አጠቃላይ ሂሳብ የሚይዘው ከቀረጥ የሚሸሽ ገዘብ ነው። ይሄም የትላልቅ ኩባንያዎች የቀረጥ አለመክፈል ነው።

ከ1960ዎቹ ጀምሮ ላለፉት አርባ ዓመታት አፍሪካ በህገ-ወጥ መልኩ የወጣው ገንዘብ ወደ 1 ትሊሊየን ዶላር ይገመታል። በእርግጥ ይሄ ተመን የማያካትታቸው አጠራጣሪ አሀዞች በመኖራቸው-ገንዘቡ ከተባለው ሊበልጥ እንደሚችል ሬይመንድ ቤከር ይናገራሉ።

በዚህ ጥናት መሰረት ኢትዮጵያ ከ16 ቢሊየን ዶላር በላይ ገንዘብ የሸሸ ሲሆን ከአፍሪካ በ13ኛ ደረጃ ትገኛለች። ባለፉት ሶስት ዓመታት ደግሞ በኢትዮጵያ የታየው የገንዘብ የህገ-ወጥ የገንዘብ ሽሽት ከሌሎች አመታት በጣም የባሰ ነው። በ2001ዓም ከሃገር የሸሸው ገንዘብ የጠቅላላ የአገሪቱን አመታዊ የመንግስት በጀት ይስተካከላል። 3.25 ቢሊዮን ዶላር ከአገር ሸሽቷል።

ለንጽጽር ያህል ጎረቤት ኬንያ ከ7-8 ቢሊየን ዶላር (22ኛ) ጅቡቲ 1 ቢሊየን ዶላር (45ኛ) ኤርትራ 117 ሚሊዮን ዶላር (51ኛ) ደረጃን ይዘዋል።

በአፍሪካ ከፍተኛ ገንጸብ በህገ-ወጥ መልኩ የሚወጣባት አገር ናይጀሪያ ስትሆን 241 ቢሊየን ዶላር ግብጽ 131 ቢሊዮን ደቡብ አፍሪካ 74 ቢሊየን ዶላር በመሆን ከ1-3 የለውን ስምን በበጎ የማያስጠራ ሰንጠረዥ ተቆናጠዋል። ይሄ ገንዘብ ደግሞ የሚጓዘው--በጥናቱ መሰረት--ወደ አደጉ አገሮች ነው። እንዴት? ሬመንድ ቤከር ያብራራሉ።

“በወጭና ገቢ ንግድ ዋጋዎች ላይ የሃሰት ደረሰኝ በመቁረጥ፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ VAT ፣ የገቢና የጉምሩክ ቀረጦችን ማጭበርበር የታወቁ መንገዶች ናቸው”

ከአንድ አገር ገንዘብ ለማሸሽ ዋነኛው መንገድ የወጭና ገቢ ንግድን ዋጋዎች በሃሰት ማጭበርበር ነው። ይሄ የሚደረገው ከውጭ የሚገባ ምርትን ዋጋ ከእውነተኛው ዋጋው በመጨመርና፤ የወጭ ምርትን ዋጋ ሆን ብሎ ማሳነስ ነው።

ይሄ ማለት በሚገባ ቋንቋ። እንበል አንድ ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ የቡና ነጋዴ ከሆነና ቻይና አገር ካለ ድርጅት ስሚንቶ የሚያስገባ ነው እንበል፤ በቀላሉ ለመረዳት።

ከዚያ ኢትዮጵያዊው ነጋዴ ከቻይና ስሚንቶ ሲያስገባ፣ እንበል የስሚንቶው ዋጋ 1 ሚሊዮን ዶላር ቢሆን፤ ዋጋ ሲስማሙ 1.2 ሚሊዮን ዶላር ብለው ድረሰኝ ይቆርጡለታል። ከዚያ ኢትዮጵያዊው ነጋዴ የ1.2 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ለቻይናዊ የንግድ አጋሩ ይልካል። ቻይናዊ ነጋዴው ደግሞ የራሱን 1 ሚሊዮን ዶላር ከወሰደ በኋላ የቀረውን 200ሽህ ዶላር በደንበኛው የውጭ የባንክ ሂስብ ቁጥር ያስገባዋል።

በዚህ መልኩ ኢትዮጵያዊው ነጋዴ 200ሽህ ዶላር የውጭ ምንዛሬ በአንድ የገበያ ልውውጥ አሸሸ ማለት ነው።

ይሄ ሁኔታ ደግሞ በአገር ውስጥ የውጭ ምንዛሬ ችግር ከማምጣቱ፣ የሃገር ሃብት ከመሸሹ፣ በተጨማሪ የስሚንቶ ዋጋን ያላግባብ ይጨምራል።

ይሄው ነጋዴ ወደ ውጭ ቡና ሲልክ ደግሞ፤ ዋጋውን ይቀንስና እንዲሁ ዋጋው በተሰበረ ደረሰኝ ቡናውን ይልካል። በዚህም አገር ማግኘት ያለባትን የውጭ ምንዛሬና የገቢ ቀረጥ በውጭ አገር የባንክ ሂሳብ ቁጥሩ ያስቀራል ማለት ነው።

በዚህ መልኩ ነው በርካታ የህገ-ወጥ ገንዘብ ከድሆች አገሮች ወደ ሀብታም አገሮች የሚተላለፈው።

ሬመንድ ቤከር ይሄ ይቅር የማይባል እውነት ነው። አሁን ባለንበት የ21ኛው ክፍለ-ዘመን መጀመሪያ መታየት የሌለበት አስነዋሪ ሀቅ ነው ይላሉ።

ቤከር የሚሰሩበት Global Financial Integrity ድርጅት ከአፍሪካ አገሮች ጋር ይህንን ወንጀል ለማስቆም አብሮ በመስራት ላይ ይገኛል። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ኢሲኤ እንዲሁም የገንዘብና የልማት ሚኒስትሮች ጋር በአንድነት አፍሪካ የህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ልትቆጣጠር የምትችልበትን መንገድ ለማብጀት ይንቀሳቀሳል።

የጥምረት ስራው- ገና በንግግር ደረጃ ላይ ይገኛል። አፍሪካ የገንዘብ ዝውውርን የሚከታተል ኮሚሽን እንድታቛቁምና የአፍሪካ መሪዎች አንድ የመወያያ አጀንዳ አድርገው መፍትሄ ለማብጀት ንግግር እንዲጀምሩ ጥረት ተጀምሯል።

ከዚያም በላይ አገሮች የጉምሩክ ቀረጥ አሰባሰባቸውን ማቀላጠፍና በቴክኖሎጂ ማገዝ ይኖርባቸዋል። የገቢ ቀረጥ አሰባሰባቸውንም ከአለም አቀፍ የቀረጥ ሰብሳቢዎች ጋር ሊመሳከር የሚችልና፤ መረጃ መለዋወጥ የሚያስችል አሰራር መዘርጋትን ይጠይቃል።

ፈጥኖ መረጃ መለዋወጥ መቻል፣ ነጋዴዎችና የንግድ ድርጅቶች በሃገር ውስጥና በውጭ ያላቸውን የገቢና ወጭ ሰንጠረዥ መመልከት የሚያስችል የመረጃ መስመር ከፍተኛ ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል ባለሙያዎች ይመክራሉ።

ሆኖም ችግሩ ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውሩ የሚከናወነው፤ በጽሁፍ በሚደረግ ስምምነት ሳይሆን ብዙውን ጊዜ በቃል ስምምነት በመሆኑ፤ ወንጀለኞቹን ለመያዝ ከባድ ያደርገዋል።

የአለም አቀፉ ማህበረሰብ በተለይ ያደጉት አገሮች የገንዘብ ዝውውር መረጃን በማደግ ላይ ላሉ አገሮች ካካፈሉ፤ ተባብሮ ችግሩን ለመቀነስ መስራት እንደሚቻል ግሎባል ፋይናንሻል ኢንተግሪቲ ተስፋ ጥሏል።

XS
SM
MD
LG