በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኢትዮጵያ እና ዩናይትድ ስቴትስ ለርዳታ እህል ውጤታማ ሥርጭት እና ቁጥጥር በጋራ ለመሥራት እንደተግባቡ መንግሥት ገለጸ


የለጋሽ ተቋማት የርዳታ እህል፣ ውጤታማ በኾነ መልኩ ለተረጂዎች የሚደርስበትንና ቁጥጥር የሚደረግበትን መንገድ በጋራ ለማመቻቸት፣ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋራ መግባባት ላይ መደረሱን፣ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም፣ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኰንን፣ ባለፈው ሳምንት፣ ከዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ጋራ ባደረጉት ውይይት፣ ከሰብአዊ ርዳታ አቅርቦት ጋራ በተያያዘ የተፈጠሩ ችግሮችን መፍታት በሚቻልበት ጉዳይ ላይ መወያየታቸውን አውስተዋል፡፡

በሌላ በኩል፣ በትግራይ ክልል፣ ለአስቸኳይ ምግብ ፈላጊዎች የተላከ 86 ሺሕ ኩንታል ስንዴ፣ እንዲሁም ከፍተኛ መጠን ዘይት እና ጥራጥሬ፣ በተለያዩ አካላት እንደተዘረፈ፣ ይህን ጉዳይ ለማጣራት በክልሉ የተቋቋመው ኮሚቴ አስታውቋል፡፡

የፌዴራል መንግሥት በበኩሉ፣ በፌዴራሉ እና በክልል አካላት ተፈጽሟል የተባለውን የተቀነባበረ ዘረፋ በማጣራት ላይ እንደኾነ ቢገልጽም፣ ዝርዝር መረጃ ግን አልሰጠም፡፡ ኾኖም፣ ዩኤስ-ኤአይዲ እና የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ ለኢትዮጵያ የሚያደርጉትን የምግብ ድጋፍ በጊዜያዊነት ማቆማቸው፣ ሚሊዮኖችን ይጎዳል፤ በሚል፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ኮምዩኒኬሽን መሥሪያ ቤት መቃወሙ ይታወሳል፡፡

በሌላ ዜና፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ አራት ሀገራት፣ የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎችን፣ በ10 ቀናት ውስጥ በዐዲስ አበባ ማደራደር እንዲጀምሩ፣ ኢጋድ መወሰኑን፣ አምባሳደር መለስ ገልጸዋል፡፡

ሙሉ ዘገባውን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።

XS
SM
MD
LG