የኢትዮጵያ የሠላም ውይይት ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙን የዲፕሎማቲክ ምንጮችን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ሮይተርስ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ያላቸው የዲፕሎማቲክ ምንጮቹ፣ በደቡብ አፍሪካ ነገ ይጀመራል የተባለው ውይይት ከሎጂስቲክስ ዝግጅት ጋር በተያያዘ እንዲዘገይ ተደርጓል ብለዋል፡፡
እስካሁን ተለዋጭ ቀን እንዳልተቆረጠም ጠቁመዋል ሲልም ዘገባው አክሏል።
ይሁን እንጂ፣ የአፍሪካ ኅብረት፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ መንግሥት እና የህወሓት ባለሥልጣናት፣ የውይይቱ ጊዜ መዘግየቱን በተመለከተ እስካሁን በይፋ ያሉት ነገር የለም፡፡
ይህን በማስመልከት ከኢትዮጵያ መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረትም ሊሳካልን አልቻለም፡፡
በተያያዘ ዜና አፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መሃማት ዛሬ ባወጡት መግለጫ፣ ኅብረቱ ላቀረበው የሰላም ውይይት ግብዣ ሁለቱም ወገኖች ያሳዩትን ቁርጠኝነት አድንቀዋል፡፡
በሌላ በኩል፣ ዩናይትድ ስቴትስ በአፍሪካ ኅብረት ለሚመራው የሠላም ሂደት ያላትን ድጋፍ ገልጻለች።