ኢትዮጵያ ውስጥ ለ19 ወራት በተካሄደው ጦርነት ወቅት የተቀበሩ ፈንጂዎች በአፋር ሰሜን-ምዕራብ አካባቢ ላሉ እረኞች ከአስከፊው ድርቅ በተጨማሪ ሌላ ራስ ምታት ሆኖባቸዋል።
በተቀበሩ ፈንጂዎች ምክንያት የህጻናትና የእንስሳት ህይወት በመቀጠፍ ላይ ነው። በኢትዮጵያ መንግስትና በአጋሮቹ በአንድ ወገን እና በትግራይ ሃይሎች በሌላ ወገን ሲካሄድ የነበረው ጦርነት ጋብ ብሎ ሊሆን ይችላል። በምዕራብ አፋር የሚገኙ እረኞች ግን በህይወት ለመቆየት ትግል ላይ ናቸው።
በአደገኝነቱ የተመዘገብ ድርቅ በአፍሪካ ቀንድ በመከሰቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ እንስሶች ረግፈዋል። በተዋጊዎቹ ተቀብረው የተተዉት ፈንጂዎች ይህን አደጋ ይበልጥ አወሳስበውታል።
የከብት አርቢው ሃሰን አረብቲ ሃሰን የ 4 ዓመት ልጅ በተቀበረ ፈንጂ ተጎድታለች። ከብቶቹም በፈንጂው እያለቁ ነው። “የተቀበሩ ፈንጂዎች በየቦታው አሉ። እላያቸው ላይ እየቆሙ ብዙ ከብቶች አልቀዋል። ፍየሎች የረግጡታል፣ ይፈነዳል።” ብሏል።
የተቀበሩ ፈንጂዎች እና ሌሎች ዓይነት ፈንጂዎች በብዛት ከመገኘታቸው የተንሳ ፈንጂዎቹ የታሸጉበትን የእንጨት ሳጥን ለሌሎች ነገሮች ግንባታ ማዋል የተለመደ ሆኗል። የዘጠኝ ዓመቱ አሊ ኡመር እንዳለው የ 10 ዓመት ጓደኛው ከእርሱ ጋር ፍየል ጥበቃ ላይ ሳሉ በተቀበረ ፈንጅ ሕይወቱን አጥቷል።
“ከጓደኛዬጋ ፍየሎቹን ጥበቃ ነበር የወጣነው። ጓደናዬ ግን ህይወቱን አጣ። እንጨት ወደ ፈንጂዎቹ እየወረወረ እየተጫወተ ነበር። አንዱን ብድግ አድርጉ ወደ መሬት ወረወረው።”
አሊም ጉዳት ደርሶበት ነበር። አባቱ ኡመር ሃዴቶ እንደሚሉት የተቀበሩትን ፈንጂዎች ፍራቻ ውሃ ያለበት ቦታ ሄደው መቅዳት አልቻሉም። “እዚህ ሰውንም ሆነ እንስሳትን ችግር ላይ የጣለ ከባድ ድርቅ አለ። ማኅበረሰቡ ምን ማድረግ እንዳለበት አያውቅም። ለቤተሰቤ ምግብና ለእንስሶቹ መኖ ለመግዛት ብዙ ብር አወጣለሁ። ቀድሞ በምንኖርበት አካባቢ የተቀበሩት ፈንጂዎች ባስቸኳይ እንዲጸዱልን እንፈልጋለን።”
የአካባቢውን ሰዎች ካነጋገረ በኋላ የትኛው ወገን ነው ፈንጂውን የቀበረው የሚለውን ቪኦኤ ማረጋገጥ አልቻለም። አቶ በቀለ ጎንፋ በአዲስ አበባ የሚገኝና የፈንጂ ጉዳተኖችን የሚረዳ ትርፋማ ያልሆነ ድርጅት ኃላፊ ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት በኢትዮጵያ በሚገኙና እንደ ጭፍራ ባሉ ፈንጂ በተቀበረባቸው ቦታዎች ያሉ ሰዎች ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል።
“ቅድሚያ የሚሰጠው ለህክምና ነው። ከዛም የምክር አገልግሎትን የሚጨምር የማህበራዊ ስነልቦና እገዛ ሊሰጣቸው ይገባል። ያንን ነው ድርጅታችን በተለይ ሚያከናውነው። አጠቃላይ ህዝቡና በአካባቢው የሚገኙ ማህበረሰቦች ከተቀበረ ፈንጂ አካባቢ እንዲርቁ ስለሚያስከትለው አደጋ ትምህርት ሊሰጣቸው ይገባል።”
በጭፍራ የሚገኙ ሰዎች፣ በደርሰው አስከፊ ድርቅ ሳቢያ፣ ለእንስሶቻቸው የሚሆን መኖና ለእራሳቸው የሚሆን ውሃ ለመቅዳት ፍለጋ ከሄዱ፣ የተቀበሩ ፈንጂዎች ከሚፈጥሩት አደጋ ጋር መጋፈጥ ግድ ይሆንባቸዋል።
/የአሜሪካ ድምፅ ዘጋቢ ሄንሪ ዊልኪንስ ያጠናቀረውን ዘገባ እንግዱ ወልዴ ወደ አማርኛ መልሶታል/