በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የደህንነት ባለሞያዎች በአፍሪካ ስለተስፋፋው የጽንፈኝነት ጥቃት መከሩ


የደህንነት ባለሞያዎች በአፍሪካ ስለተስፋፋው የጽንፈኝነት ጥቃት መከሩ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:12 0:00

የደህንነት ባለሞያዎች፣ በተለይም በሳሃል ክልል፣ አሳሳቢ በሆነ ሁኔታ እየጨመረ የመጣውን የእስላማዊ ተዋጊዎችን ጥቃት ጨምሮ፣ በአፍሪካ እየተባባሰ ስለመጣው የጽንፈኞች ጥቃት ለመምከር በዚህ ሳምንት ሴኔጋል ውስጥ ተሰብስበዋል፡፡

ባላፈው አስርት ዓመታት አፍሪካ ውስጥ የሚገኙ እስላማዊ አማጽያንን ጥቃት ለመዋጋት ስፍር ቁጥር የሌለው ወታደራዊ እርዳታ እና ዶላሮች ጎርፈዋል፡፡ ስለችግሩ መንስኤና መፍትሄ ለመምከርም በርካታ ፎርሞችና ስልጠናዎች ተካሂደዋል፡፡ ችግሩ ግን እየባሰበት ሄደ እንጂ የትም አልሄደም፡፡

ከእስላማዊ አማጽያን ጋር ተያይዞ በአህጉሪቱ የደረሰው ሞት ባላፈው ዓመት በ50 ከመቶ ያህል አሻቃቧል።ከ19 ሺህ በላይ ሰዎች የሞቱ ሲሆን ፣ አብዛኞቹ በምዕራብ ሳህል ክልል መሆናቸውን ከአፍሪካ ስትራቴጂክ ጥናቶች ማዕከል የተገኘው መረጃ አመልክቷል፡፡ ጥቃቱ መልክአምድራዊ አቅጣጫ ይዞ በምዕራብ አፍሪካ የባህር ዳርቻ ወደ ሚገኙት ግዛቶችና የቻድ ሀይቅ ተፋሰሶች ወደ መሳሰሉት ሌሎቹ አዳዲስ ክልሎች እየተስፋፋ ነው፡፡

በምዕራብ አፍሪካና ሰሃል የተባበሩት መንግሥት ጽ/ቤት ኃላፊ ጂኦቫኒ ቢሃ “በምዕራብ እና በማዕከላዊ አፍሪካ ያለው የደህንነት ሁኔታ እየተበላሸ መምጣቱ ሚስጥር አይደለም፡፡” ይላሉ፡፡

“አሸባሪ ቡድኖች ብዙና የተወሳሰቡ ችግሮች ያሉበትን ቀጠና፣ በተለይም የአካባቢውን የፖለቲካ፣ የማህበራዊ ኢኮኖሚ፣ እንዲሁም እኩልነት አለመኖርና ድክመትን እየተጠቀሙበት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ የክልሉ ፈተና፣ የክልሉ ምላሽ እንዲሰጠውም እየጠየቀ ነው፡፡” በማለት “የትኛውም አገር የአክራሪ ጽንፈኝነትና ሽብርተኝነትን ጥቃት ለብቻው አልተዋጋም” ሲሉም ቢሃ የትብብርን አስፈላጊነት አክለው ገልጸዋል፡፡

እኤአ በ2015 የተባበሩት መንግሥታት የአመጸኞችን ጥቃት ለመከላከላ፣ የጽንፈኝነት ጥቃት የመከላከያ መርሃ ግብር ነድፏል፡፡ የዚህ ሳምንቱ ስብሰባ የዚያን መርሃ ግብር በመገምገም በተናጥል የሚገኙ አካባቢዎችና መንግሥታት የመርሃግብሩን ስትራቴጂ እንዴት አድርገው በተሻለ መንገድ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚችሉ ይመለከታል፡፡

ስብሰባው የተሰናዳው በምዕራብ አፍሪካ እና ሳህል ተባበሩት መንግሥታት ጽ/ቤት፣ በስዊስ ፌደራል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ እና በሴነጋል የመከላከያና ደህንነት ከፍተኛ የጥናት ማዕክል ነው፡፡

በጋና የብሄራዊ ደህንነት ሚኒስትር አልበርት ካን ዳፓ፣ አገራቸው በምዕራብ አፍሪካ የባህር ዳርቻ ከሚገኙት አገሮች መካከል ምንም ዓይነት የሽብርተኝነት ጥቃት አስተናግዳ የማታውቅ ብቸኛ አገር መሆንዋን ተናግረዋል፡፤

ምንም እንኳ ካን ዳፓ፣ ጋና ከሽብር ጥቃት ነጻ ልትሆን ስለቻለችበት ምክንያት እርግጠኛ አለመሆናቸውን ቢያምኑም፣ የተባበሩት መንግሥታት መርሃግብር ከወጣ በኋላ አገራቸው ብሄራዊ ማዕቀፉን በመርሃ ግብሩ መሰረት ተግባራዊ ማድረጓን ሲያስረዱ

“ሥልጣን ላይ ባለው መንግሥት ብቻ የሚሆን ነገር አይደለም፡፡ እንደዚያ በፍጹም አይሰራም፡፡” ብለዋል፡፡ ዳፓ አያይዘውም “ንኡሳኑን ፓርቲ ማሳተፍ ያስፈልገሃል፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ማሳተፍ፣ የሴቶች ድርጅቶችና ወጣቶችን ማሳተፍ ያስፈልጋል፡፡ ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ጋና ጥቃትን ለመከላከል ከምታደርገው ጥረት አንዱ ለጽንፈኝነት የተጋለጡ እንደ መጠጥ ውሃ ትምህር ቤቶችና ክሊኒኮች ያሉ የማህበረሰብ ግብዓቶቹን ከጥቃት መከላከልን ያካትታል ሲሉ ካን ዳፖህ ተናግረዋል፡

ባላፈው ወር በተባበሩ መንግሥታት የልማት መርሃ ግብር የወጣው ሪፖርት ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገሮች የሽብርተኝነት ቡድኖችን ከተቀላቀሉት ውስጥ 25 ከመቶ የሚሆኑ ዋነኛው ምክንያታቸው ሥራ ፍለጋ መሆኑን አመልክቷል፡፡

ይህ ምክንያት እኤአ በ2017 ከነበረው በአራት እጥፍ ያህል ማደጉን ጥናቱ አመልክቷል፡፡ ለሽብርተኝነት ዋነኛው ምክንያት ሃይማኖት የመሆኑ ጉዳይም ከነበረበት 57 ከመቶ ቀንሶ ታይቷል፡፡ ለዚህ ማረጋገጫውም ከተመልማዮቹ መካከል ሃይማኖትን እንደመሰረታዊ ምክንያት ያደረጉት 17 ከመቶ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

በቡርኪና ፋሶ የግራናዳ አማካሪ ተቋም የደህንነት ባለሙያ የሆኑን መሃሙዱ ሳቫዶጎ ስብሰባው የተቀናጀ ምላሽ ስለማስፈለጉ ግንዛቤ ያስጨብጣል ብለው ተስፋ ማድረጋቸውን ይገልጻሉ፡፡

“እያንዳንዱ አገር ወሰን ተሻጋሪ ለሆኑ ችግሮች የራሱ የሆነ ስትራቴጂና መፍትሄ አለው፡፡ ይሁን እንጂ በጸረ ሽብርተኝነት ውጊያው ድንበሮችን መርሳት ይኖርብሃል፡፡” ያሉት ሳቫዶግ “ በአገሮች መካከል ህብረት ከሌለ፣ ግልጽ ውይይት እስከለሌ፣ ክልላዊ ወይም አህጉራዊ ምላሽ ከሌለ እጅግ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡” ብለዋል ፡፡ውይይቱ ዛሬ ሀሙስ ድረስ መቀጠሉ ተመልክቷል፡፡

XS
SM
MD
LG