በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአፍሪካ ነክ ርዕሶች


የአፍሪካ ነክ ርዕሶች
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:34 0:00

በዛሬው የአፍሪካ ነክ ርዕሶች ፕሮግራማችን ሶስት ጉዳዮችን እንመለከታለን፦

· በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት በተደርገው ጦርነት ወቅት የጦር ወንጀልና ሌሎች ሰቆቃዎች ስለመፈጸማቸው እንዲመረምር የተመደበው ዓለም አቀፍ ገለልተኛ መርማሪ ቡድን ሥራውን እንዲያቋርጥ የኢትዮጵያ መጠየቋን ባለፈው ሳምንት አንድ ሪፖርት ይፋ አድርጓል፡፡ በሮይተርስ የወጣው ሪፖርት የመርማሪ ኮሚሽኑን ሥራ ለማስቆም ያላትን አቋም መንግስታት እንዲደግፉ ኢትዮጵያ በማግባባት ላይ መሆኗን አመልክቷል፡፡

· ናይጄሪያ ሥራ ላይ ያዋለችው አዲስ የብር ኖት ሥርጭት ኢሕገመንግስታዊ ነው ቢሚል የአገሪቱ ጠቅላይ ፍ/ቤት አሮጌው ብር እስከ ያዝነው የፈረንጆች ዓመት መጨረሻ ድረስ ሥራ ላይ እንዲቆይ አዟል፡፡

· በእሥር ላይ የሚገኘው የደቡብ ሱዳኑ የመብት ተሟጋች እንዲለቀቅ አንድ አፍሪካዊ የጠበቆች ቡድን ጥሪ አድርጓል፡፡ ሞሪስ ማቢዮር ባለፈው ወር በኬንያ መዲና ናይሮቢ በጸጥታ ኃይሎች የተያዘ ሲሆን፣ ቤተሰቡ እንደሚለው ለደቡብ ሱዳን ተላልፎ ተሰጥቷል፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት በተደርገው ጦርነት ወቅት የጦር ወንጀልና ሌሎች ሰቆቃዎች ስለመፈጸማቸው እንዲመረምር የተመደበው ዓለም አቀፍ ገለልተኛ መርማሪ ቡድን ሥራውን እንዲያቋርጥ የኢትዮጵያ መጠየቋን ባለፈው ሳምንት አንድ ሪፖርት ይፋ አድርጓል፡፡ በሮይተርስ የወጣው ሪፖርት የመርማሪ ኮሚሽኑን ሥራ ለማስቆም ያላትን አቋም መንግስታት እንዲደግፉ ኢትዮጵያ በማግባባት ላይ መሆኗን አመልክቷል፡፡

የጦር ወንጀልን የሚመረምረው የገለልተኛ መርማሪዎቹ ሥራ የሚቋረጥ ከሆነ የመብት ጥሰት የተፈጸመባቸው ሰለባዎች ፍትህ እንዳያገኙ ያደርጋል፣ የተመድንም ተአማኒነት ያሳጣል ሲሉ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ድምጻቸውን አሰምተዋል፡፡

ገለልተኛ መርማሪ ቡድኑ ሥራውን እንዲያቋርጥ የሚጠይቀውን የኢትዮጵያ አቋም በመቃወም፣ የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ም/ቤት ኢትዮጵያ የምታቀርበውን ሃሳብ ውድቅ እንዲያደርግ 63 የሚሆኑ ዓለም አቀፍ የሲቪልና ሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ጠይቀዋል፡፡ ድርጅቶቹ በጋራ የጻፉት ደብዳቤ በሂውማን ራይትስ ዎች ድህረ ገጽ ላይ ተለቋል፡፡

ደብዳቤውን ከፈረሙት አንዱ የሆነው አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ የኮሚሽኑን ሥራ ማቋረጥ ወደፊት ትልቅ ችግር የሚፈጥር ነው ብሏል፡፡

በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የአፍሪካ ቀንድ ሃላፊ የሆኑት ሱአድ ኑር እንደሚሉት ሙከራው የሚጠቅመው በኢትዮጵያ ያለውንና ሥር የሰደደውን ከህግ ተጠያቂነት የማምለጥ ባህል ነው፡፡

“ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተፈጸመባቸው ሰለባዎች ፍትህ እንዳያገኙ ያደርጋል፡፡ ይህም ከፍተኛ ጥሰት በተፈጸመበት ግጭት ውስጥ የተፈጸመ ጾታዊ ጥቃትን ይጨምራል” ብለዋል ሱአድ ኑር።

የመርማሪ ኮሚሽኑ የተቋቋመው በኢትዮጵያ መንግስትና በትግራይ ኃይሎች መካከል ጦርነቱ በተጀመረ በዓመቱ ነበር፡፡ የመብት ተሟጋች ቡድኖች ሁለቱም ወገኖችች ሰቆቃ፣ ጅምላ ግድያ፣ ያለፍርድ ማሠር እና አስገድዶ መድፈር የመሰሉ ወንጀሎችን ፈጽመዋል ሲሉ ይከሳሉ፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ከጅምሩም የኮሚሽኑን ምርመራ የተቃወመ ሲሆን፣ ከዓመት በፊት ለኮሚሽኑ የሚመደበው በጀት እንዲቆም ሞክሮ በቂ ድምጽ ሳያገኝ ቀርቷል፡፡

ኮሚሽኑ የሚያደርገው ምርመራ ከመጠናቀቁ ስድስት ወር በፊት እንዲቆም የኢትዮጵያ የመፍትሄ ሃሳብ ልታቀርብ ነው ሲሉ ዲፕሎማቶችን ባለፈው ሳምንት ለሮይተርስ ዜና ወኪል ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ለሮይተርስ ሪፖርት ቀጥተኛ መልስ ባይሰጥም ከሶስት ሣምንት በፊት በተደረገው የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ ላይ ግን የኢትዮጵያው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ሃሳቡን የሚያረጋግጥ ንግግር አድርገዋል፡፡

“መርማሪ ኮሚሽኑ በአፍሪካ ኅብረት መሪነት የሚደረገውን የሰላም ሂደትና የሰላም ስምምነቱን ተግባራዊነት በአሉታዊ ትርክት የሚበክል ነው፡፡ ብሔራዊ ተቋማት የሚያደርጉትን ጥረትም ያዳክማል” ሲሉ ተናግረዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን።

የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ንግግር በጽሁፍ ለአንዳንድ መገናኛ ብዙሃን የተሰራጨ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ የኮሚሽኑ ሥራ እንዲቋረጥ የውሳኔ ሃሳብ ማዘጋጀቷንና በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ላለው የተመድ የሰብዓዊ ም/ቤት ዓመታዊ ስብሰባ ላይ እንደሚቀርብ ያትታል፡፡ የአፍሪካ ሕብረትም የውሳኔ ሃሳቡን እንዲደግፍ ጥሪ ያደርጋል፡፡ በጽሑፍ የተቀመጠውን ይህን ሃሳብ ግን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በንግግራቸው ወቅት አላሰሙትም፡፡

“መጥፎ ምሳሌ የሚሆን ነው” በሚል ኢትዮጵያ ግፊቷን እንድታቆም ለማግባባት ምዕራባዊያን ዲፕሎማቶች ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውን የሮይተርስ ሪፖርት አመልክቷል፡፡

በአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ ላይ በነበረ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተመድ ዋና ጸሓፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በም/የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ንግግር ላይ ምን አስተያየት እንዳላቸው በቪኦኤ ተጠይቀው ነበር፡፡

“እኔ መመስከር የምችለው አንድ ነገር፣ የተመድ የሰብዓዊ ሥራ ከሰላም ሂደት ጋር የሚስማማ ሥራ መሆኑን ነው” ብለዋል ጉቴሬዝ።

በአስር ሺህዎች፣ ምናልባትም በአንዳንዶች ግምት በመቶ ሺህዎች ሕይወት የቀጠፈውን ጦርነት የአፍሪካ ኅብረት ባለፈው ጥቅምት በሰላም እንዲቋጭ አድርጓል፡፡

አድ ኑር እንደምትለው ግን ሰላም እንዲሰፍን ከተፈለገ፣ ፍትህና ተጠያቂነት መኖር አለበት፡፡

ሁለቱም ወገኖች ከፍተኛ የመብት ጥሰት ፈጽመዋል፣ መንግስት ደግሞ ረሃብን እነደጦር መሣሪያ ተጠቅሟል የሚለውንና ባለፈው መስከረም የወጣውን የኮሚሽኑ ሪፖርት የኢትዮጵያ መንግሥት ውድቅ አድርጓል፡፡

ናይጄሪያ

ናይጄሪያ ሥራ ላይ ያዋለችው አዲስ የብር ኖት ሥርጭት ኢ-ሕገመንግስታዊ ነው ቢሚል የአገሪቱ ጠቅላይ ፍ/ቤት አሮጌው ብር እስከ ያዝነው የፈረንጆች ዓመት መጨረሻ ድረስ ሥራ ላይ እንዲቆይ አዟል፡፡

የጠቅላይ ፍ/ቤቱ ያለፈው ዓርብ ውሳኔ የመጣው 16 የሚሆኑ አገር ገዢዎች አሮጌዎቹ የ 200፣ 500 እና 1000 ሺህ ብር ኖቶች ግልጋሎት ላይ እንዲቆዩ ከጠየቁ በኋላ ነው፡፡ መንግስት ለብር ለውጡ የሠጠው ግዜ ስድስት ወር ብቻ ነበር፡፡ መንግስት የ500 እና 1000 ኖቶችን እንዲቀር ያደረገው ወንጀልንና ጠለፋን እንዲሁም አስመስሎ ማተምን ለማስቀረት፤ በተጨማሪም በዝውውር ውስጥ ያለውን ትርፍ ጥሬ ገንዘብ ለመቀነስ መሆኑን ይናገራል፡፡

ኔክስቲየር በተባለው ተቋም የኢኮኖሚ ባለሙያ የሆኑት ንዱ ንዎኮሎ መንግስት የጠቅላይ ፍ/ቤቱን ተዕዛዝ ይቀበላል የሚል ተስፋ የለኝም ይላሉ፡፡

“ሥራ አስፈጻሚው ጠቅላይ ፍ/ቤቱ የሚለውን ሰምተናል ሊል ይችላል፡፡ የተባለውንም እንፈጽማለን ሊል ይችላል፡፡ የሚፈጅባቸውን ግዜ ከወሰዱ በኋላ ማነው ፍ/ቤት አቁሞ የተባላችሁትን አላደረጋችሁም፣ በተግባር ወደ መተርጎም አልገባችሁም የሚላቸው?” ብለዋል ንዎኮሎ።

መንግስት ያስቀመጠውን የግዜ ገደብ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሲሽር ፕሬዝደንት ቡሃሪ ትዕዛዙን አልተቀበሉም ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱ የፈላጭ ቆራጭነት ምልክት ነው ብሏቸው ነበር፡፡

ደቡብ ሱዳን

በእሥር ላይ የሚገኘው የደቡብ ሱዳኑ የመብት ተሟጋች እንዲለቀቅ አንድ አፍሪካዊ የጠበቆች ቡድን ጥሪ አድርጓል፡፡

ሞሪስ ማቢዮር ባለፈው ወር በኬንያ መዲና ናይሮቢ በጸጥታ ኃይሎች የተያዘ ሲሆን፣ ቤተሰቡ እንደሚለው ለደቡብ ሱዳን ተላልፎ ተሰጥቷል፡፡

የኬያም ሆነ የደቡብ ሱዳን ባለሥልታናት በመብት ተሟጋቹ መያዝ ጉዳይ ላይ አስተያየት አይሰጡም፡፡ በመሆም የደህንነቱ ሁኔታ አሳሳቢ ሆኗል፡፡

የፓን አፍሪካ ጠበቆች ኅብረት ለኬንያና ለደቡብ አፍሪካ መንግስታት በሞሪስ ማቢዮር መጥፋት ጉዳይ ላይ ክስ አቅርቧዋል፡፡

የኅብረቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶናልድ ደያ ለቪኦኤ እንደተናገሩት ክሱ የቀረበው የስደተኞችን ጉዳይ ለሚያየው ለምሥራቅ አፍሪካ ፍ/ቤት ነው፡፡

“ስለዚህ እኛ የምንለው በአስቸኳይ ተለቆ የሕክምና ምርመራ እንዲያደርግ ነው። ካለዛ ጥፋት አለበት ብለው በያዙት ጉዳይ መብቱ በሚጠበቅለት ፍ/ቤት ክስ እንዲመሠርቱ ነው” ብለዋል ደያ።

የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ የመብት ቡድኖች ጉዳዩን ሲያወግዙ፣ ኬንያ የተመድንና የአፍሪካ ኅብረትን የስደተኞች መብት ጥሳለች ሲሉ ይከሳሉ፡፡

በደቡብ ሱዳን የጸጥታ ኃይሎች ጥበቃ ሥር ያለው “ሰማያዊው ቤት” ተብሎ የሚጠራው ቦታ የመንግስት ነቃፊዎች የሚታገቱበት፣ የሚሰቃዩበትና የሚጠፉበት ቦታ እንደሆነ የመብት ተሟጋቾች ይናገራሉ፡፡

የሞሪስ ማቢዮር ቤተሰቦችም የመብት ተሟጋቹ “በሰማያዊው ቤት” እንደተያዘ ያምናሉ፡፡

XS
SM
MD
LG