በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በአንጎላ ምርጫ ገዢው ኤምፒኤልኤ እየመራ ነው



በአንጎላ ምርጫ ገዢው ኤምፒኤልኤ እየመራ ነው
please wait

No media source currently available

0:00 0:02:35 0:00

ትናንት በአንጎላ የተካሄደው ምርጫ ቆጠራ ዛሬ በመካሄድ ላይ ሲሆን፤ በብሄራዊ ምርጫ ቦርዱ የወጡ ጊዜያዊ ውጤቶች እንደሚያሳዩት ገዢው ኤምፒኤልኤ በመምራት ላይ ነው። ሆኖም ተቃዋሚው ዩኒታ ጊዜያዊ ውጤቱን “ተአማኒነት የለውም” ሲል አጣጥሎታል።

ሮይተርስ የኮሚሽኑን መግለጫ ጠቅሶ እንደዘገበው፣ እስከ አሁን 86 በመቶ የሚሆነው ድምጽ የተቆጠረ ሲሆን፣ ሃገሪቱ ከፖርቹጋል ቅኝ አገዛዝ ነጻ ከወጣችበት እአአ 1975 ጀምሮ በሥልጣን ላይ ያለው ኤምፒኤልኤ ከመራጩ ሕዝብ 66.65% በመቶውን፤ ተቃዋሚው ዩኒታ ደግሞ 33.85 ድምጽ አግኝቷል።

ዘገባው አክሎ እንዳመለከተው የምርጫ ኮሚሽኑ አጠቃላይ የድምጽ ሰጪዎች ቁጥርና አካባቢያዊ የውጤት ሥርጭትን የመሰሉ ቁልፍ የሆኑ የአሃዝ መረጀዎችን አላቀረበም።

ተቃዋሚውን ዩኒታ ወክለው ለምክትል ፕሬዚዳንትነት የሚወዳደሩት አቤል ቺቩኩቩኩ ውጤቱ “የሚታመን አይደለም” ብለዋል።

“ከሁሉም የሃገሪቱ ግዛቶች የድምጽ መስጫ ጣቢያዎቻችን ያገኘነው ግዜያዊ ውጤት እያሸነፈን እንደሆነ እያመለከቱ ነው” ብለዋል ቺቩኩቩኩ። ውጤቱ ከተረጋገጠ፣ አብዛኛውን መቀመጫ የሚይዘው ኤምፒኤልኤ ፕሬዚዳንት ጃኦ ሎሬንሶን ሌላ ሁለተኛ የ5 ዓመት የሥልጣን ዘመን ይጨምርላቸዋል።

የፖለቲካ ተንታኞች የትናንቱን ምርጫ ለተቃዋሚው ዩኒታ እስከ አሁን ያልተገኘ ጥሩ የማሸነፊያ አጋጣሚ ነበር ሲሉ ይናገራሉ። ለዚህም አንጎላውያን “ከሃገሪቱ የነዳጅ ምርት ሃብት ድርሻ ተጠቃሚ አላደረገንም” በሚል በገዢው ኤምፒኤልኤ ላይ ቅሬታቸው እየጨመረ መምጣቱን እንደ ምክንያት ይጠቅሳሉ።

የዛሬው የኮሚሽኑ ውጤት እወጃ በአስደናቂ ሁኔታ ፈጣን ነው ተብሏል። እአ.አ በ2017 በተካሄደው ምርጫ ውጤቱ የታወጀው ከሁለት ሳምንታት በኋላ ነበር።

ዩኒታ እና ኤምፒኤልኤ ሃገሪቱ ከፖርቹጋል ነጻ ከወጣችበት እአአ 1975 ጀምሮ ተፎካካሪዎችንና ባላንጦች ሆነው ቆይተዋል። ሁለቱ ወገኖች ያዝ ለቀቅ እያደረጉ ለ25 ዓመታት የእርስ በርስ ጦርነት አካሂደዋል። በዚህም በመቶ ሽህ የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።

የ2017ቱም ሆነ የአሁኑ ምርጫ ሁከትን አላስከተሉም። የጸጥታ ጥናቶች ተቋም የተሰኘው አካል ግን "ኤምፒኤልኤ የምርጫውን ውጤት በማጭበርበር አሸንፌያለሁ ካል ብጥብጥ የከተላል" ብሏል።

“ድምጽ ሰጪዎች የሆነውን ሊያምኑ አልቻሉም” ሲሉ አንጎላዊው የፖለቲካ ተንታኝ ክላውዲዮ ሲልቫ ዛሬ ለሮይተርስ ተናረዋል። በድምጽ ሰጪዎች ከውጤት ሰንጠረዥ ላይ የተነሱ ፎቶዎች የምርጫ ኮሚሽኑ ካሳወቀው ውጤት ጋር የሚውቃረኑ ናቸው" ባይ ናቸው።

XS
SM
MD
LG