መንግሥት፣ አጋቾቻቸውን ተከታትሎ ርምጃ አለመውሰዱ ግራ እንዳጋባቸው፣ ዓሊዶሮ በተባለ ቦታ ታግተው እና ገንዘብ ከፍለው የተለቀቁ ሾፌሮች እና ቤተሰቦቻቸው ተናገሩ።
በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ምዕራብ ሸዋ ዞን ዓሊዶሮ በተባለ ቦታ፣ ሰኔ 10 ቀን 2015 ዓ.ም.፣ እርሱን ጨምሮ 79 የሚሆኑ አሽከርካሪዎች እና ረዳቶች፣ ራሱን የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ብሎ በሚጠራው ታጣቂ ታግተው እንደነበር፣ ከእገታው 500ሺሕ ብር ከፍሎ የተለቀቀ አንድ ታጋች ተናግሯል፡፡
በምሥራቅ ጎጃም ዞን ማቻከል ወረዳ ዐማኑኤል ከተማ፣ አባቱ በጉሊት ሥራ እንደሚተዳደሩ የገለጸው አንድ ታጋች፣ አባቱ ቤታቸውን ለግለሰብ አስይዘው ተበድረው እንዳስለቀቁት ይናገራል። ገንዘቡን መመለስ ካልቻሉም ቤታቸውን እንደሚያጡ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
በዚኹ ከተማ ጡረተኛ መምህር እንደኾኑ የገለጹልን አንድ የታጋች አባት፣ 900ሺሕ ብር ከግለሰብ ተበድረው ቀሪውን ከወዳጅ እና ዘመድ ሰብስበው አንድ ሚሊዮን ብር ከፍለው ልጃቸውን ማስለቀቃቸውን ገልጸዋል፡፡ ብድሩን በወቅቱ ካልከፈሉ፣ ቤታቸውን ሸጠው ለመክፈል እንደሚገደዱ፣ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት፣ ለመንግሥት ኮምዩኒኬሽንስ አገልግሎት ከፍተኛ ሓላፊዎች የእጅ ስልካቸው ላይ ብንደውልም ባለመነሣቱ አስተያየታቸውን ማካተት አልቻልንም።
የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ዓለም አቀፍ ቃል አቀባይ ኦዳ ተርቢ ግን፣ ሰሞኑን ስለ ጉዳዩ ከአሜሪካ ድምፅ ተጠይቀው፣ ታጣቂዎቻቸው እንዲህ ዐይነቱን ድርጊት እንዳልፈጸሙ አስተባብለው፣ በተጠቀሰው አካባቢ የተለያዩ ኃይሎች እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ መናገራቸው ይታወሳል።
ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።