በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኬንያ የሽብር ጥቃት ፍርደኞች የእስር ጊዜያቸው ተቀነሰ


በኬንያ የሽብር ጥቃት ፍርደኞች የእስር ጊዜያቸው ተቀነሰ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:02 0:00

· “አሸባሪዎች ወደዚኽ አገር እንዲሳቡ የሚያደርግ ውሳኔ ነው” - የጸጥታ ተንታኝ

ከስምንት ዓመታት በፊት እ.አ.አ በ2015 በጋሪሳ ዩኒቨርሲቲ በተፈጸመውና የ148 ሰዎችን ሕይወት በቀጠፈው የሽብር ጥቃት ተሳትፈዋል፤ በሚል የ41 ዓመታት እስር የተፈጸመባቸው ኹለት ፍርደኞች፣ የእስር ዘመናቸው ወደ 25 ዓመት ተቀንሶላቸዋል፡፡

የከፍተኛው ፍ/ቤት ዳኛ ሲሲሊያ ጊቷ፣ ሃሳን ኤዲን ሃሳንና ሞሐመድ አብዲ አቢካር የተባሉት ፍርደኞች፣ “የአል ሻባብ አባል ነበሩ፤” የሚለውን ክሥ ውድቅ አድርገውላቸዋል፡፡ “የሽብር ወንጀል ለመፈጸም በማሴር እና ወንጀሉን በመፈጸም” በሚሉት ላይ ግን ጥፋተኝነታቸውን አጽንተዋል፡፡ በዚኽም ምክንያት፣ የእስር ዘመናቸው ከ41 ወደ 25 ዓመት ተቀንሷል፡፡

መቀመጫቸውን ናይሮቢ ያደረጉት የጸጥታ ተንታኝ ሪቻርድ ቱያ እንደተቹት፣ ፍርዱ በሽብርተኝነት ላይ የሚደረገውን ትግል የሚጎዳ ነው፡፡ “አሸባሪዎች ወደዚኽ አገር እንዲሳቡ የሚያደርግ ውሳኔ ነው፡፡ ምክንያቱም፣ አሸባሪዎች ትርፍ እና ኪሳራቸውን አስልተው የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ ቅጣቱ የሚቀንስ ከኾነ፣ ይህ አገር ለእነርሱ አዋጭ ነው ማለት ነው፤” ብለዋል ቱያ፡፡

አንድ የታችኛው ፍ/ቤት እ.አ.አ በ2019፣ ኹለቱን ፍርደኞች፣ የሽብር ወንጀል ለመፈጸም በማሤር እንዲሁም የሽብር ወንጀል በመፈጸም፣ በ25 ዓመት ተኩል በተጨማሪም፣ የአል ሻባብ አባል በመኾናቸው በ15 ዓመት ተኩል እስራት ቀጥቷቸው ነበር፡፡ ኾኖም፣ ባለፈው ዓርብ ዳኛዋ ቅጣቱን ሲቀንሱ እንደተናገሩት፣ ዐቃቤ ሕግ ፍርደኞቹ የአል ሸባብ አባል መኾናቸውን የሚያሳይ ማስረጃ አላቀረበም፡፡

የጸጥታ ተንታኙ ቱያ፣ ፍርዱ፥ የ148 ሟች ቤተሰቦችን ስሜት ያልጠበቀ ነው፤ ይላሉ፡፡ “እንደ እኔ ከኾነ ማሾፍ ነው የተያያዙት፡፡ ኾኖም፣ በፍ/ቤቱ ማመካኘት አይቻልም፤ ምክንያቱም ፍርድ ቤቱ የሚያየው የቀረበለትን ማስረጃ ነው፤” ሲሉ ተናግረዋል ቱያ፡፡

ዳኛዋ፣ የ25 ዓመቱን ቅጣት በአጸኑበት ወቅት እንደተናገሩት፣ የዐቃቤ ሕግ የኹኔታዊ ማስረጃ አቀራረብ፣ ፍርደኞቹ፣ ጥቃቱን ስለማቀዳቸውም ኾነ ጥቃቱን ስለመፈጸማቸው ያለጥርጥር አረጋግጧል፡፡

ከስምንት ዓመታት በፊት፣ አራት ታጣቂዎች፣ ወደ ጋሪሳ ዩኒቨርስቲ በመግባት እና ተኩስ በመክፈት 148 ሰዎችን ገድለዋል፡፡ መሠረቱን በሶማልያ ያደረገው አል ሻባብ በኋላ ላይ በአወጣው መግለጫ፣ ጥቃቱን ኬንያ ላይ የፈጸመው አገሪቱ ወደ ሶማልያ ሠራዊቷን በመላኳ ነው፡፡

XS
SM
MD
LG