በዐዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተተገበረው የቤት ግብር ተመን ማሻሻያ፥ ሕጋዊ መሠረት እንደሌለው፣ አንድ የሕግ ባለሞያ ተናገሩ፡፡
የዐዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት የግልግል ተቋም ዲሬክተር አቶ ዮሐንስ ወልደ ገብርኤል፣ ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት የግል አስተያየት፣ የከተማዋ አስተዳደር የቤት ግብር ተመንን የጨመረው፣ ከ45 ዓመት በፊት የወጣውን የመሬት ኪራይ እና የሕንፃ ግብርን የሚመለከት ደንብን በማሻሻል እንደኾነ ቢገልጽም፣ አግባብነትን ተከትሎ ባለመኾኑ ሕጋዊነት እንደሌለው አስረድተዋል፡፡
የዐዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው፣ ለመንግሥት ብዙኃን መገናኛ በሰጡት ቃለ መጠይቅ፣ የቤት ግብር መጠኑን ለመጨመር የደንብ ማሻሻያ እንዳልተደረገ ገልጸዋል፡፡ የሚከፈለውን የቤት ግብር መጠን ለማሻሻል ግን፣ ከ45 ዓመት በፊት የወጣው ደንብ ይፈቅዳል፤ ብለዋል፡፡ በዐዲሱ ተመን መሠረት የቤት ግብራቸውን እየከፈሉ ያሉ ነዋሪዎች በአንጻሩ፣ ውሳኔው፥ የኑሮ ውድነቱን ያገናዘበ አይደለም፤ ኅብረተሰቡንም ለችግር እየዳረገው ይገኛል፤ ሲሉ ቅሬታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በዐዲስ አበባ ከተማ፣ በአንዱ የወረዳ ጽ/ቤት የተተመነላትን የቤት ግብር ከፍላ ስትወጣ ያገኘናት ፎዝያ አሕመድ፣ የተለያዩ ችግሮች ባሉበት በዚኽ ወቅት፣ የቤት ግብር መጠንን መጨመር አግባብ አይደለም፤ ብላለች፡፡
ኮንዶሚኒየም እየተባሉ በሚጠሩ የጋራ መኖሪያ ቤቶች፣ 44 ካሬ ቤት እንዳላቸው የተናገሩት አቶ ደመላሽ አበራ ደግሞ፣ በዐዲሱ ተመን መሠረት፣ 2ሺሕ300 ብር እንደከፈሉ ገልጸው፣ “ውሳኔው አሁን ያለብንን ችግር ከግምት ያስገባ አይደለም፤” ብለዋል፡፡ስሜ እንዳይጠቀስ ያሉን ሌላው አስተያየት ሰጪ፣ የቤት ግብር መጠን ጭማሬው፣ የኑሮ ውድነትን ያባብሳል፤ ብለዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ በቅርቡ ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ማብራሪያ የሰጡት የዐዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ውሳኔው የኑሮ ውድነትን ያባብሳል፤ ብዬ አላምንም በማለት ተከላክለዋል፡፡ ከንቲባዋ፣ የከተማዋ አስተዳደር የኅብረተሰቡን ኑሮ ለማረጋጋት፣ በተለያዩ ዘርፎች እስከ ሰባት ቢሊዮን ብር የሚደርስ ድጎማ እንደሚያደርግ ተናገረው፣ የቤት ግብር ተመን ማሻሻያው የተደረገውም፣ ከዚኽ በፊት ግብር የማይከፍሉትን ነዋሪዎች፣ ወደ ግብር ሥርዐቱ ለማስገባት እና ፍትሐዊ የሀብት ስርጭት ለመፍጠር እንደኾነ አመልክተዋል፡፡
አሁን የተደረገውን የቤት ግብር መጠን ጭማሪ የሚተቹት የሕግ ባለሞያ አቶ ዮሐንስ ወልደ ገብርኤል በበኩላቸው፣ የከተማዋ አስተዳደር ይህን ማድረግ የሚችለው፣ ከ45 ዓመት በፊት የወጣውን ዐዋጅ እና ደንብ በማሻሻል ቢኾንም፣ “ይህን ግን አላደረገም፤” ብለዋል፡፡
ዐዋጅ ቁጥር 80/1968 እና ደንብ ቁጥር 36/1968 መሻሻል የሚገባቸው፣ ከቤት ማከራየት ጋራ ተያይዞ በደርግ ዘመን በሥራ ላይ የነበረው ፖሊሲ፣ በኢሕአዴግ ዘመን በመቀየሩ ጭምር እንደኾነ፣ አቶ ዮሐንስ ይገልጻሉ፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአንጻሩ፣ የቤት ግብር መጠኑን ለማሻሻል ብለን ያሻሻልነው ደንብ የለም፤ ካሉ በኋላ፣ ከ45 ዓመት በፊት የወጣው ደንብ፣ አጠቃላይ የክፍያ መጠኑን በየጊዜው ማሻሻል እንደሚቻል ያስቀምጣል፤ ብለዋል፡፡ ይህን መነሻ በማድረግም፣ የቤት ግብር መጠኑ መሻሻሉን የጠቀሱት ከንቲባዋ፣ አሁን ያለው የኢኮኖሚ እና የንግድ እንቅስቃሴ፣ እንዲሁም የኑሮ እና የገቢ ኹኔታም ታሳቢ መደረጉን አመልክተዋል፡፡
ከንቲባዋ፣ ስለማሻሻያው አፈጻጸም ሲናገሩም፣ ከተሰላው የቤት ግብር መጠን፣ የመኖሪያ ቤቶች 50 ከመቶውን፣ የንግድ ቤቶች ደግሞ 75 ከመቶውን ብቻ እንዲከፍሉ መደረጉን አስረድተዋል፡፡ ለአሜሪካ ድምፅ አስተያየት የሰጡ ነዋሪዎች ግን፣ ይህ ውሳኔ ኅብረተሰቡን ለችግር ዳርጎታል፤ ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁን አስተያየት ሰጪ ይህን ብለዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ በመንግሥታዊው የቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት ማብራሪያ፣ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ ከቤት ግብር ነፃ የሚደረጉበት፣ አለያም ከሚያገኙት ዝቅተኛ ገቢ ጋራ የሚመጣጠን ዝቅተኛ የቤት ግብር እንዲከፍሉ የሚያደርግ ሥርዐት ለመዘርጋት እየሠራን ነው፤ ብለዋል፡፡