በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአውሮፓ ሚኒስትሮች በኢትዮጵያ ያለውን የሰላም መሻሻል አወድሰዋል


የአውሮፓ ሚኒስትሮች በኢትዮጵያ ያለውን የሰላም መሻሻል አወድሰዋል
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:51 0:00

የአውሮፓ ሚኒስትሮች በኢትዮጵያ እያደረጉት ባለው ጉብኝት በኢትዮጵያ ያለውን የሰላም መሻሻል ያወደሱ ሲሆን - በአንጻሩ ያለፍትህ ዕርቅ አይኖርም ሲሉ የፈረንሳይ እና የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አሳስበዋል፡፡

ለሁለት ዓመታት የዘለቀው ጦርነት መቆምን በመደገፍ የፈረንሳይ እና የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በኢትዮጵያ ጉብኝት እያደረጉ ሲሆን ሚኒስትሮቹ በትላንትናው ዕለት ባደረጉት ንግግር ያለፍትህ ዕርቅ ሊመጣ አይችልም ብለዋል።

የፈረንሳይ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካትሪን ኮሎና እና የጀርመኗ አናሌና ባየርቦክ የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን የጀመሩት የህወሓት ኃይሎች ከባድ መሳሪያቸውን ማስረከብ መጀመራቸው ይፋ ባደረጉ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።

የፈረንሳይ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኮሎና ከጀርመኗ አቻቸው ጋር በጋራ ባደረጉት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ “ግጭት ቆሟል፣ እርዳታ ይደርስባቸው ያልነበሩ ቦታዎች ድጋፍ እየደረሰ ነው። እንዲሁም ተዋጊዎቹ መሳሪያ እየመለሱ ነው” በማለት በፌዴራል መንግሥት እና በህወሓት መሃከል ያለውን የሰላም ሽግግር ሂደት አበረታተዋል።

ይሁን እንጂ ሁለቱም ሚኒስትሮች በግጭቱ ወቅት የተፈጸሙ በደሎችን የሚያይ ፍትሃዊ የሽግግር ሥርዓት እንዲመሰረት አሳስበዋል።

የጀርመኗ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ባርቦክ በበኩላቸው “እኛ ጀርመናዊያን እና ፈረንሳዮች እርቅ በአንድ ሌሊት እንደማይከሰት እናውቃለን። ነገር ግን በወንጀል ጥቃት ተጎጂ የሆኑ ሰዎች ፍትህ የሚያገኙበት ተስፋ ከሌለ ዕርቅ እና ዘላቂነት ያለው ሰላም አይኖርም” ሲሉ ተናግረዋል።

ሁለቱ ሚኒስትሮች ትግራይን ለምን ሳይጎበኙ እንደቀሩ ከጋዜጠኞች ጥያቄ የቀረበላቸው ሲሆን፤ የጀርመኗ ባርቦክ “ይሄ የአዲስ ነገር ጅማሬ ነው ወደፊት የባለቤትነት ጥያቄ የሚነሳባቸውን ቦታዎችም ጭምር የምንጎበኝ ይሆናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን መንግሥታቸው ወንጀሎች ሳይቀጡ እንደማያልፉ እንደሚያረጋገጥ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ አስታውቀዋል።

XS
SM
MD
LG