በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በ“ጉማ ሽልማት” ፍጻሜ በእስር ሦስት ቀናትን ያሳለፈው የፊልም ባለሞያው ዮናስ ብርሃነ ተፈታ


በ“ጉማ ሽልማት” ፍጻሜ በእስር ሦስት ቀናትን ያሳለፈው የፊልም ባለሞያው ዮናስ ብርሃነ ተፈታ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:09 0:00

የ“ጉማ ሽልማት” አዘጋጅ ዮናስ ብርሃነ መዋ፣ ከሦስት ቀናት እስር በኋላ በዋስ የተፈታ ሲኾን፣ ፖሊስ፥ “ሕዝብን በመንግሥት ላይ የሚያነሣሣ የፖለቲካ መልዕክት ማስተላለፍ” በሚል ክሥ እንደጠረጠረው ታውቋል፡፡

አዘጋጁ ዮናስ ብርሃነ መዋ፣ ዓርብ ሰኔ 2 ቀን 2015 ዓ.ም.፣ በስካይላይት ሆቴል የተካሔደው የሽልማት ሥነ ሥርዐት እንደተጠናቀቀ ከምሽቱ 5፡30 አካባቢ፣ ከባለቤቱ ጋራ ነበር በቁጥጥር ሥር ውሎ የነበረ ሲሆን ፤ ወደ ቦሌ ፖሊስ መምሪያ ከተወሰዱ በኋላ፣ ባለቤቱ ወዲያው ስትለቀቅ፣ ዮናስ በፖሊስ ጣቢያው እንዲቆይ ተደርጓል፡፡

ፖሊስ፣ ዮናስን በቁጥጥር ሥር ያዋለበት ምክንያት፣ 9ኛው የጉማ ሽልማት ሥነ ሥርዓት በተካሔደበት ወቅት፣ ከአንዲት የዝግጅቱ ተሳታፊ ጋራ በመተባበር፣ “ሕዝብን በመንግሥት ላይ የሚያነሣሣ ፖለቲካዊ መልዕክት አስተላልፈዋል፤” በሚል እንደኾነ፣ የአሜሪካ ድምፅ፣ ጉዳዩን በቅርበት ሲከታተሉ ከነበሩና ስማቸው እንዳይጠቀስ ከጠየቁ የቅርብ ምንጮች አረጋግጧል፡፡

ዮናስ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር በዋለበት ምሽት፣ “የፖለቲካ መልዕክት አስተላልፋለች፤” ያላትን ግለሰብ እንዲያቀርብ ጠይቆት እንደነበረም፣ ምንጮቻችን አረጋግጠዋል፡፡

በቲክ ቶክ የቪዲዮ ማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይ፣ የተለያዩ መልዕክቶችን በማስተላለፍ የምትታወቀው ፍላጎት አብርሃም፣ በ9ኛው የጉማ ሽልማት ሥነ ሥርዐት ላይ የታየችበት አለባበሷ እና የተጠቀመችው ሜካፕ፣ ከነበረችበት አዳራሽ ሳትወጣ፣ በማኅበራዊ የትስስር መድረኮች በስፋት እየተሠራጨ መነጋገሪያ ኾኗል፡፡

በቲክቶክ ስሟ “የልጅ ማኛ” በመባል የምትታወቀው ፍላጎት፣ ቬሎ ለብሳ ከቬሎው ውስጥ በደረቷ ዙሪያ አረንጓዴ ቢጫ እና ቀይ ጥለት የሚታይ ሲኾን፣ ፊቷ ላይ የተሠራችው የሜካፕ ጥበብ ደግሞ፣ “ግንባሯ በጥይት ተመትቶ እየደማ እንደሆነ፣ እንዲሁም አፏ እንደተሸበበ” የሚያመልክት ነው፡፡

ይኹን እንጂ፣ ፍላጎት፥ የአለባበሷንና ሜካፕዋን ስለምንነት ባታብራራም፣ ፖሊስ የጉማ አዋርድ አዘጋጅ ዮናስ ብርሃነን፣ በቀጣዩ ዕለት ቅዳሜ፣ ሰኔ 3 ቀን፣ በዐዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ ችሎት ባቀረበበት ወቅት፣ ከፍላጎት ጋራ በመተባበር፣ “ሕዝብን በመንግሥት ላይ በማነሣሣት” ወንጀል እንደጠረጠረው ጠቅሶ፣ የምርመራ ጊዜ እንደጠየቀ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ጉዳዩን የተመለከተው ፍርድ ቤቱ፣ ዮናስ የተጠረጠረበት ወንጀል፣ በእስር ለማቆየት በቂ ምክንያት እንደማይኾን ገልጾ፣ በአምስት ሺሕ ብር ዋስ እንዲፈታ ወስኗል፡፡

የዮናስ ቤተሰቦች፣ የዋስትናውን ገንዘብ አስይዘው መፈታቱን ቢጠብቁም፣ ዮናስ፣ በተለምዶ 3ኛ ተብሎ ወደሚጠራው ወደ ዐዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ተወስዶ፣ ሁለት ቀናትን በፖሊስ ጣቢያው ካሳለፈ በኋላ፣ ዛሬ ረፋዱን፣ በባለቤቱ የመታወቂያ ዋስ ብቻ፣ ከእስር መለቀቁን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡

የዮናስን መፈታት ያረጋገጡት ወላጅ አባቱ አቶ ብርሃነ መዋ፣ ልጃቸው የታሰረበት ምክንያት፣ በሽልማት ሥነ ሥርዐቱ ላይ፣ አንዲት አርቲስት ካሳየችው አለባበስ እና ሜካፕ ጋራ እንደሚገናኝ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዶር. ዳንኤል በቀለ፣ የዮናስ ብርሃነን መታሰር አስመልክተው፣ ትላንት ሰኔ አራት ቀን፣ በማኅበራዊ ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፣ “ድርጊቱ ሕገ ወጥ እና ተቀባይነት የሌለው ነው፤” ሲሉ ኮንነዋል፡፡

ቅዳሜ ዕለት የተፈቀደው የዋስትና መብት ሳይከበር፣ ለተጨማሪ እስር መዳረጉንም ተችተዋል፡፡ ዶር. ዳንኤል፣ “ሌላ የቴሌቭዥን ባለሞያ፣ በኪነ ጥበብ ሽልማት ዝግጅት ላይ፣ ጭንቅላቷ በጥይት መቁሰሉን እና አፏ በሽቦ ክር መታሰሩን የሚያሳይ የጥበብ ሥራ በማሳየቷ ምክንያት፣ የፊልም ባለሞያው ዮናስ ብርሃነ መዋ መታሰሩ፣ ሕገ ወጥ እና ተቀባይነት የሌለው ነው፤” ሲሉ ገልጸዋል። ጥበብ፥ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ አንዱ አካል እና ክፍል እንደኾነ ያመለከቱት ዶር. ዳንኤል፣ ያለምንም ቅድመ ኹኔታ በአስቸኳይ እንዲለቀቅም፣ በትላንቱ መልዕክታቸው አሳስበው ነበር፡፡

የፊልም ባለሞያው እና የ”ጉማ ሽልማት” አዘጋጅ ዮናስ ብርሃነ፣ በአሁኑ ወቅት ከእስር ቢለቀቅም፣ ስለ ጉዳዩ፣ ከዐዲስ አበባ ፖሊስ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ፣ የቃል አቀባዩ ስልካቸው ባለመሥራቱ ሊሳካልን አልቻለም፡፡

XS
SM
MD
LG