በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አምነስቲ በትግራይ ተፈፀሙ ስለተባሉ የፆታ ጥቃቶች ሪፖርት አወጣ


በሰሜን ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል መቀሌ በሚገኝ ሆስፒታል ቃለ ምልልስ ባደረገበት ወቅት። የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዘገባ ረቡዕ ነሐሴ 11 ቀን 2021
በሰሜን ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል መቀሌ በሚገኝ ሆስፒታል ቃለ ምልልስ ባደረገበት ወቅት። የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዘገባ ረቡዕ ነሐሴ 11 ቀን 2021

አምነስቲ ኢንተርናሽናል በትግራዩ ጦርነት የተሳተፉ የኢትዮጵያና የኤርትራ መከላከያ ሠራዊት አባላት እንዲሁም የአማራ ክልል ልዩ ኃይልና የፋኖ ሚሊሺያዎች በልጃገረዶችና በሴቶች ላይ ፈፅመዋቸዋል ያላቸውን ፆታዊ ጥቃቶችን ያጠናቀረበትን ጥናት ይፋ አድርጓል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል በትግራዩ ጦርነት የተሳተፉ የኢትዮጵያና የኤርትራ መከላከያ ሠራዊት አባላት እንዲሁም የአማራ ክልል ልዩ ኃይልና የፋኖ ሚሊሺያዎች በልጃገረዶችና በሴቶች ላይ ፈፅመዋቸዋል ያላቸውን ፆታዊ ጥቃቶችን ያጠናቀረበትን ጥናት ይፋ አድርጓል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ ባወጣው መግለጫ እንዲህ ያሉትን ህገ ወጥ ድርጊቶችና ወሲባዊ ጥቃቶችንም ከግምት በማስገባት ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን አስታውሷል።

“አምነስቲ የመረጃ ምንጭ ያደረገው በሱዳን ያሉት ስደተኞችን እዚያውም ውስጥ በማይካድራ ወንጀል ፈፅመው ከሸሹት ጋር ተደባልቀው የሚገኙትን ብዙ የህወሃት ሚሊሺያዎችና የእርዳታ ሠራተኞችን ነው” በማለት የመንግሥቱ መግለጫ ሪፖርቱን ኮንኗል።

የኤርትራ መንግሥትም ክሡን ውድቅ አድርጓል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ከየካቲት እስከ ሰኔ 2013 ድረስ ያካሄደውን ጥናት ያጠናቀረው ጾታዊና ተያያዥ ወሲባዊ ጥቃቶች ተፈጽሞብናል ያሉ 63 ሰዎች በማነጋገር መሆኑን ገልጿል፡፡

ከእነዚህ ውስጥ 15ቱን በሱዳን መጠለያ ካምፖች በአካል ቀርቦ እንዳነጋገረ አምነስቲ ገልፆ 48 የሚሆኑትን ደግሞ ያነጋገረው በርቀት ደህንነቱ በተጠበቀ የስልክ መስመር መሆኑን አስታውቋል።

ከየካቲት እስከ ሚያዚያ በነበሩት ወራት ውስጥ 1288 የሚሆኑ የፆታ ጥቃትና የተፈፀመባቸውና የተደፈሩ ሴቶች ወደ ህክምና ጣቢያዎች መሄዳቸውን የሚያሳይ መረጃ ከጤና ተቋማት ባለሙያዎች መሰብሰቡን አመልክቷል።

በሱዳን የመጠለያ ጣቢያ ያሉትን ጨምሮ አዲግራትና ሽሬን በመሳሰሉ ከተሞች የሚገኙትንና የጥቃቱ ሰለባ እንደሆኑ የተነገረ ሴቶችን ሲንከባከቡ ነበሩ የተባሉ የህክምና ባለሙያዎችና የእርዳታ አገልግሎት ሰጭዎችንም ማነጋገሩንም አምነስቲ ገልጿል።

የአምነስቲ ኢንተርናሽናልን ሪፖርት ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት ባወጣው መግለጫ በማናቸውም ሁኔታ ውስጥ ወሲባዊ ጥቃትን የሚያወግዝ መሆኑን ገልፆ “ትግራይ ክልል ውስጥ በተካሄደው ግጭት ወቅት አንዳንድ የሠራዊቱ አባላት በግልፅ የተሰጣቸውን መመሪያና ደንቦችን በሚፃረሩ ተግባራት ላይ መሳተፋቸውን በመገንዘብ መግለጫ ማውጣቱን ጠቅሷል። እንዲህ ያሉትን ህገ ወጥ ድርጊቶችና ወሲባዊ ጥቃቶችንም ግምት በማስገባት ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እርምጃዎችን ወስዷል። ወደፊትም ጥቃት ፈጻሚዎችን ለፍርድ የማቅረቡን ይቀጥልበታል” ብሏል።

የኢትዮያ መንግሥት ባወጣው መግለጫ ከተደረሰበት አጠቃላይ ድምዳሜ አንፃር “ይህ አኀዝና አቀራረብ በቂ ነው?” የሚል ጥያቄ አንስቷል። አምነስቲ የመረጃ ምንጭ ያደረገው ሱዳን ያሉ ስደተኞችን ከመካከላቸውም ማይካድራ ውስጥ ወንጀል ፈፅመው ከሸሹት ጋር ተደባልቀው የሚገኙትን ነው ብዙ የወያኔ ሚሊሺያዎችም ሰፍረዋል” ብሏል።

ከአሜሪካ ድምፅ የእንግሊዝኛው ፕሮግራም ባልደረባ ስቲቨን ሚለር ጋር ቃለ መጠይቅ ያደረጉት የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የቀውስ ጉዳዮች ከፍተኛ አማካሪና የሪፖርቱ ተባባሪ ፀሃፊ ዶናቴላ ሮቬራ “ይህ በመካከለኛው ምሥራቅ እና በአፍሪካ የጾታዊ ጥቃቶችንና ጦርነቶች ላለፉት 20 ዓመት እንደመረመረ ሰው እንዲህ ያለ የከፋ ሁኔታ ገጥሞኝ አያውቅም” ብለዋል። በሪፖርታቸውም ላይ እንደተዘገበው የትግራይ ሴቶችና ልጃገረዶች የጦርነት ማካሄጃ በተደረገ ጥቃት መድፈርና ወሲባዊ ጥቃት ተፈፅሞባቸዋል” ብለዋል።

“በሴቶቹ ላይ የተፈፀሙት ብዙዎቹ ወሲባዊ ወንጀሎች ከባድና አስደንጋጭ ናቸው። ሴቶች በቡድን የተደፈሩ፣ ለወሲብ ባርነት የተዳረጉ፣ የፆታ አካላትን በሾሉና በስለት ማቆሳሰል፣ በተለያዩ የማሰቃያ መንገዶች መጉዳት፣ ማንነታቸውን የሚያጎድፍ ስድብ፣ የሞት ማስፈራሪያና ዛቻዎች የደረሰባቸው በመሆኑ ዘላቂ የአካልና የሥነልቦና ጉዳት ደርሶባቸዋል” ሲል አምነስቲ በሪፖርቱ አመልክቷል። “ብዙዎቹ አድራጎቶች በጦር ወንጀልነት ሊያስጠይቁና በሰው ልጅ ላይ ሊፈፀሙ የማይችሉ ናቸው”ም ብሏል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በመግለጫው “አምነስቲ ኢንተርናሽናል በቀደሙ ሪፖርቶቹ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ስሜት ቀስቃሽ ጥቃቶችንና ስም የማጥፋት ዘመቻቸዎችን ወደ ማካሄድ ያዘነበለ ይመስላል” ብሏል። በተለይ “በአንዳንዶቹ የምሥራቅ አፍሪካ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሠራተኞች የሙያ ሥነምግባርና ገለልተኝነት ላይ ጥርጥሬ እንዳለው” አመልክቷል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል በበኩሉ ለኢትዮጵያና ኤርትራ ለሚገኙ መሪዎችና በየደረጃው ላሉ መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች በጥናቱ ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ መጠየቁን ጠቅሶ ምላሽ አለማግኘቱን ገልጿል።

በሌላ በኩል ለሪፖርቱ ምላሽ እንዲሰጡና አስተዳደራቸው እነዚህን ድርጊቶች ለማስቆም ምን እያደረገ እንደሆነ የተጠየቁት የዋይት ኃውስ ቃል አቀባይ ጄን ሳኪም መንግሥታቸው በአካባቢው ካሉ አገሮች መሪዎች ጋር በቅርበት እየተገናኘ መሆኑን ተናግረው ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ባለውና በምናየው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት በእርግጥ ደንግጠናል፤ ይህንን በሚመለከት በዚያ አካባቢ እየሠራን ስላለው ዝርዝር ነገር ይበልጥ መረጃ ለማግኘት በእርግጠኛነት የምመራችሁ ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴራችን ነው” ብለዋል። አክለውም በባለሥልጣናቱ አማካይነት በርካታ መግለጫዎችን ማውጣታቸውን አስታውሰው ወደፊትም በይፋ ማውጣት እንደሚቀጥሉ አመልክተዋል።

በትግራይና በአጎራባቾቹ አማራና አፋር ክልሎች ውስጥ የተፈፀሙ ጥቃቶች ተጠርጣሪዎችና ተጠያቂዎችን ለመያዝና ለፍርድ ለማቅረብ ሁኔታው “ከባድ ችግር የፈጠረበት መሆኑን”ም መንግሥት በመግለጫው አስታውቋል።

ይህን ዘገባ መሰረት በማድረግ የሪፖርቱ ተባባሪ ፀሃፊና የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምሥራቅ አፍሪካ አጥኚ አቶ ፍስሃ ተክሌ ከአሜሪካ ድምፅ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል። ሙሉው ቃለ ምልልስ ተያይዟል።

ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ያድምጡ።

አምነስቲ በትግራይ ተፈጸሙ ስለተባሉ የጾታ ጥቃቶች ሪፖርት አወጣ
please wait

No media source currently available

0:00 0:14:37 0:00


XS
SM
MD
LG