በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአርቲስት አለማየሁ እሸቴ የቀብር ስነ ስርዓት ተፈጸመ


የአርቲስት አለማየሁ እሸቴ የቀብር ስነ ስርዓት ዛሬ ተፈጸመ
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:04 0:00

የአርቲስት አለማየሁ እሸቴ የቀብር ስነ ስርዓት ዛሬ ተፈጸመ

በልብ ሕመም ነሐሴ 27 ቀን 2013 ዓ.ም በ80 ዓመቱ በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው አርቲስት አለማየሁ እሸቴ በዛሬው ዕለት የቀብር ስነ ስርዓቱ ተፈጽሟል፡፡

ከቀብር ስነስርዓቱ ቀደም ብሎ፣ የሙያ አጋሮቹ፣ የመንግስት ባለስልጣናት እና የጥበብ አፍቃሪያን በተገኙበት በመስቀል አደባባይ የአስክሬን ሽኝት ስነ ስርአት ተከናውኗል፡፡ በዚህ ዝግጅት ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉ የሙያ አጋሮቹ እንዲሁም የመንንግስት ባለስልጣናት አርቲስቱ በዘመን ተሸጋሪ ስራዎቹ ለሀገር እና ለማሕበረሰብ ስላበረከተው አስተዋጽኦ በማንሳት ተምሳሌትነቱን መስክረዋል፡፡

በዝግጅቱ ላይ ንግግር ካደረጉ ታዳሚያን መካከል የሆነው ባለቅኔ እና ፀሐፌ ተውኔት አያልነሕ ሙላቱ፣ ለረዥም ጊዜ የሚያውቀውን ወዳጁ የነበረውን አርቲስት አለማየሁን በኢትዮጵያ የዘመናዊ ሙዚቃ ጀማሪ ሲል ይገልጸዋል፡፡

“አለማየሁ ብዙ ሰው እንደሚለው፣ የዘመናዊ ሙዚቃ ፈጣሪ ነው ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ ዘመናዊነትን ወደ ኢትዮጵያ አመጣ ቢባል ሀሰት አይደለም፡፡ እዚህ ጋር ግን ለእናት ኢትዮጵያ የሚዘምር፣ አብሯት የሚያለቅስ፣ አብሯት የሚያንጎራጉር፤ እናቱም፣ እህቱም፣ ልጁም አድርጎ የሚያይ ትልቅ ቀስቃሽ፣ አስተማሪ የሆኑ ስራዎችን የሰራ ሰው ነው፡፡ እናም አብሮን የቀረውን የዚህን ታላቅ ሙዚቀኛ ድምጽ (ሙዚቃ) ይዘን፣ ዛሬም ነገም ከነገ ወዲያም አብሮን ስለሚኖር በዚሁ እንድንጽናና እጠይቃለሁ” ብሏል ባለቅኔ እና ፀሐፌ ተውኔት አያልነሕ ሙላቱ በአስከሬን ሽኝት ዝግጅቱ ላይ ስለ አርቲስት አለማየሁ ሲናገር፡፡

የሽኝት ስነስርዓቱን ያዘጋጀው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ አርቲስት አለማየሁን ሀገሩን በቅንነት በማገልገል ለሌሎች ትምህርት የሆነ የጥበብ ሰው እንደነበር መስክረዋል፡፡

“ለሀገሩ ዘመን ተሸጋሪ ስራ የሰራ፣ ሀገሩን በቅንነት ያገለገለ፣ ለሀገሩ በትልቅ ፍቅር የተጋ፣ በስራዎቹ ምክንያት ከመቃብር በላይ ሲዘከር፣ ሲታወስ ይኖራል እንጂ አይሞትም” ያሉት ወ/ሮ አዳነች፣ “ዛሬ አለማየሁ እሸቴ አልሞተም፤ በስራዎቹ ምክንያት ህያው ሆኖ ይኖራል” ብለዋል፡፡ አክለውም “በአለማየሁ ህልፈተ ሕይወት ብናዝንም፣ ከሱ ሕይወት እና በሕይወቱ ከሰራቸው ስራዎች የሙያ ባልደረባዎቹም ሆነ ሌሎች አገልጋዮች ብዙ መማር ይችላሉ” ሲሉ ተምሳሌትነቱን አውስተዋል፡፡

አርቲስት ዓለማየሁ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ በቆየው የሙዚቃ ሕይወቱ በተለያዩ ዘርፎች ላይ ያተኮሩ ከ400 በላይ ሙዚቃዎችን ሰርቶ ለሕዝብ አበርክቷል፡፡ ከሰራቸው ሙዚቃዎች አብዛኛው በራሱ የተደረሱ እንደሆኑም ይነገርለታል፡፡

ኢትዮጵያዊው ኤልቪስ ፕሪስሊ በመባል የሚታወቀው አርቲስት አለማየሁ፣ እርሱን ጨምሮ ከ50 በላይ ድምጻዊያን በተሳተፉበት ስለኢትዮጵያ የተሰኘ አልበም ላይ የመጨረሻ የጥበብ ድምጹን ቢያሳርፍም አልበሙ ታትሞ ለሕዝብ ሲቀርብ ለመመልከት ግን አልታደለም፡፡ ከአባቱ አቶ እሸቴ አንዳርጌ እና ከእናቱ ወ/ሮ በላይነሽ የሱፍ በ1933 ዓ.ም የተወለደው አርቲስት ዓለማየሁ፣ በ80 ዓመቱ ይህችን ዓለም በሞት ተሰናብቷል፡፡

የአርቲስቱ የቀብር ስነስርዓትም ቤተሰቦቹ፣ ወዳጅ ዘመዶቹ እና አድናቂዎቹ በተገኙበት ዛሬ ጻጉሜ 2 ቀን 2013 ዓ.ም ከቀኑ 8 ሰዓት ላይ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል፡፡ ለወላጆቹ ብቸኛ ልጅ የነበረው አርቲስት አለማየሁ እሸቴ የአራት ወንድና የሶስት ሴት ልጆች አባት ሲሆን፤ ስድስት የልጅ ልጆችን ማየቱንም ከህይወት ታሪኩ ለማወቅ ተችሏል፡፡

XS
SM
MD
LG