በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አል-ሻባብ በሶማሊያ የኢትዮጵያ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት አደረሰ


ባኮል ክልል፣ ሶማሊያ
ባኮል ክልል፣ ሶማሊያ

· የአል-ሻባብ የድል መግለጫ “ፕሮፓጋንዳ ነው” - በሶማሊያ የኢትዮጵያ አምባሳደር

አል-ሻባብ፣ በደቡባዊ ምዕራብ ሶማሊያ በምትገኘው ባኮል ግዛት፣ የኢትዮጵያን ወታደሮች ጭነው ይጓዙ በነበሩ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች አጀብ ላይ፣ ባለፈው ሳምንት እሑድ፣ መስከረም 6 ቀን 2016 ዓ.ም. ጥቃት ማድረሱን፣ የሶማሊያ መንግሥት ባለሥልጣናት አስታወቁ።

ጥቃቱ የተሰነዘረው፣ በሁለት ወታደራዊ የጭነት አጀብ ላይ ሲኾን፣ አንደኛው ከሶማሊያ፣ ይድ ከተማ ወደ ዋጂድ ከተማ፤ ሁለተኛው ደግሞ፣ ከኤል ባሬድ ከተማ ወደ ኹዱር ከተማ ይጓዙ እንደነበር ተገልጿል። የኢትዮጵያ ወታደሮች፣ በዋጂድ እና ኹዱር ከተሞች የጦር ሠፈር አላቸው።

አንድ የሶማሊያ ባለሥልጣን፣ የአካባቢው ኃይሎች፣ ከኤል ባርዴ ተነሥቶ ወደ ኹዱር ይጓዝ የነበረውን ወታደራዊ ጭነት አጅበውት እንደነበር ገልጸዋል።

ውጊያው የተጀመረው፣ በአካባቢው ደፈጣ ጥሎ ይጠባበቅ የነበረው አል-ሻባብ ጥቃት ካደረሰ በኋላ እንደኾነ፣ የኹዱር ከተማ ከንቲባ ኦማር አብዱላሂ መሐመድ፣ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

“ውጊያው የተጀመረው፣ ፀረ ሰላም ኃይሎች ወደ ዋጂድ እና ኹዱር ይጓዙ በነበሩ የኢትዮጵያ እና የሶማሌ ወታደራዊ መኪናዎች ላይ ቦምብ በማፈንዳት ማጥቃት ከጀመሩ በኋላ ነው፤” ያሉት ከንቲባው፣ ኾኖም ወታደሮቹ፣ በመልሶ ማጥቃት ኹኔታውን እንዳረጋጉት አስረድተዋል።

መሐመድ አክለውም፣ ታጣቂዎቹ እስከ 50 የሚደርሱ ተዋጊዎቻቸውን እንዳጡ አስታውቀዋል።

ሌላ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የሶማሌ ክልል ባለሥልጣን በበኩላቸው፣ በዋጂድ ለሚገኙ የኢትዮጵያ ወታደሮች፣ ቁሳቁሶችን ለማድረስ ይጓዝ የነበረው የጭነት አጀብ፣ ከባድ የደፈጣ ጥቃት እንደደረሰበት፣ ለአሜሪካ ድምፅ ገልጸዋል።

የጭነት መኪናው፣ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ፣ ከይድ እንደተነሣ የጠቀሱት ባለሥልጣኑ፣ ሌሊቱን፣ ከዋጂድ በስተሰሜን 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ባኮ መንደር አቅራቢያ እንዳሳለፈም አመልክተዋል።

“ጎሕ ሲቀድ፣ የጭነቱ አጀብ ወደ ዋጂድ ጉዞውን ቢቀጥልም፣ አድፍጠው ይጠብቁ በነበሩ የአልሻባብ ታጣቂዎች ጥቃት ደርሶበታል፤” ያሉት ባለሥልጣኑ፣ “ሁለት መኪናዎች በፍንዳታ እንደተመቱ ሰምተናል፤” ሲሉ ኹኔታውን አብራርተዋል። ከዚያ በኋላ ለሰዓታት ውጊያ እንደተካሔደም ተናግረዋል።

ለደፈጣ ጥቃቱ ሓላፊነቱን የወሰደው አል-ሻባብ ባወጣው መግለጫ፣ 167 የኢትዮጵያ ወታደሮችን መግደሉን፣ ወታደራዊ መኪናዎችን ማወደሙንና የጦር መሣሪያዎችንና ጥይቶችን መያዙን አስታውቋል።

በሁለቱም ወገኖች የተገለጹት የጉዳት አኀዞች፣ በገለልተኛ አካል አልተረጋገጡም።

የአል-ሻባብን የድል መግለጫ፣ በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች እንደተመለከቱ የገለጹት፣ በሶማሊያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙክታር መሐመድ፣ መግለጫው፥ “ፕሮፓጋንዳ ነው” ሲሉ፣ ለአሜሪካ ድምፅ ምላሽ ሰጥተዋል።

አል-ሻባብ፣ የኢትዮጵያን ጦር ለማጥቃት ሙከራ ሊያደርግ እንደሚችል የተቀበሉት አምባሳደሩ፣ ነገር ግን፣ “ከዐሥር ደቂቃ በላይ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ላይ መተኮስ እንኳን አይችሉም፤” ሲሉ፣ አጸፋውን የመቋቋም ዐቅም እንደሌለው ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሠራዊት የሠለጠነ፣ በሚገባ የታጠቀ እና በደንብ የተደራጀ፣ እንዲሁም አል-ሻባብን ሁልጊዜም ጠንክሮ እንደሚያጠቃ ገልጸዋል፡፡ የአል-ሻባብ መግለጫ፣ “በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያ መከላከያ ኃይሎች ላይ ከሚነዛ፣ በተለምዶ ከሚታወቅ ፕሮፓጋንዳ የዘለለ አይደለም፤” ሲሉ ድሉን አጣጥለዋል።

አል-ሻባብ በመግለጫው፣ የኢትዮጵያ ወታደሮችን፥ “የመስቀሉ ተጋዳዮች በማለት መሣለቁንም፣ አምባሳደሩ ውድቅ አድርገዋል። “እኛ እንደተባለው፣ የመስቀሉ ተጋዳዮች አይደለንም፤” ያሉት አምባሳደር ሙክታር፣ ጦራቸው እዚያ የተገኘው፣ በአፍሪካ ኅብረት እና በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ውሳኔ መሠረት፣ የሶማሊያን ሕጋዊ መንግሥት እና በአገሪቱ ሰላም ለማስፈን የሚያደርገውን ጥረት ለመደገፍ እንደኾነ አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ፣ በአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ተልዕኮ ሥር ኾነው የሚያገለግሉና ከሞቃዲሾ መንግሥት ጋራ በተደረገ ስምምነት የሚንቀሳቀሱ፣ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች በሶማሊያ ውስጥ አሏት።

የደፈጣ ጥቃት የደረሰባቸው ወታደሮች፣ በአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ተልዕኮው አካል አለመኾናቸውን፣ የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸው የደኅንነት ምንጭ ተናግረዋል።

ጥቃቱ መድረሱንና ከባድ እንደነበር ያረጋገጡት እኚኹ ምንጭ፣ በአልሸባብ የተጠቀሰው ቁጥር ግን የተጋነነ እንደኾነ አብራርተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የሶማሊያ መንግሥት ወታደሮች፣ የባደወይኒን ከተማ እና ሌሎች ሦስት አነስተኛ መንደሮችን በቁጥጥር ሥር እንዳዋሉ፣ የሶማሊያ መንግሥት አስታውቋል። የአካባቢው ጦር አዛዥ መሐመድ ኑር ዓሊ ጋዳር ለአሜሪካ ድምፅ እንደገለጹት፣ አል-ሻባብ፣ ከባደወይኒ እና ሌሎች ሁለት መንደሮች ሸሽቶ የወጣው፣ ባለፈው ሳምንት እሑድ መጠነኛ ውጊያ ከተካሔደ በኋላ ነው። በአካባቢው ታጣቂዎች የተደገፈው የመንግሥቱ ጦር፣ ወደ ሌሎች ከተሞችም ይዞታውን እያስፋፋ እንደኾነም፣ ጋዳር ጨምረው ጠቁመዋል።

በሶማሊያ እየተካሔደ ባለው ዘመቻ፣ የዓለም አቀፍ አጋሮች ያላቸው ሚና፣ በአል-ሻባብ ተዋጊዎች እና ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ላይ የአየር ጥቃት ከማድረስ ያለፈ እንዳልኾነ ተገልጿል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG