በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኢንተርኔትን መገደብ የአፍሪካን ኢኮኖሚ ጎትቷል


ወጣቱ ኬኒያዊ በኢንተርኔት ካፌ ውስጥ (ናይሮቢ እኤአ 2012)
ወጣቱ ኬኒያዊ በኢንተርኔት ካፌ ውስጥ (ናይሮቢ እኤአ 2012)

አንድ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ቡድን ሰሞኑን ባወጣው ሪፖርት፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚን፣ በተለይም ከኮቪድ 19 በኋላ ተመልሶ እንዲያድግ ለማድረግ፣ አፍሪካ የበይነ መረብ ተደራሽነትን ማሳደግ ይኖርባታል ብሏል፡፡

ተሟጋቹ ቡድን እንዳመለከተው፣ በአፍሪካ የበይነ መረብ ግንኙነት ተጠቃሚዎች ቁጥር እየጨመረ ቢሆንም፣ የኢንተርኔት ተጠቃሚው ቁጥር ከአምስቱ አፍሪካውያን መካከል አንዱ ብቻ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በአንዳንድ አፍሪካ መንግሥታት የሚጣለው ከፍተኛ ቀረጥና፣ በተደጋጋሚ እንዲዘጋ የሚደረገው ኢንተርኔት አገልግሎት፣ በበይነ መረብ መስመር ላይ የሚካሄዱ የንግድ አገልግሎቶችን፣ ተስፋ እያስቆረጠ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

የበይነ መረብ፣ ወይም የኢንተርኔትኔት ማህበረሰብ ቡድን፣ በዚህ ወር ባወጣው ሪፖርት እንዳመለከተው፣ ባለፉት 8 ዓመታት ውስጥ IXP ወይም የአፍሪካ የኢንተርኔት ልውውጥ ተደራሽነት ከ19 ወደ 46 ነጥብ ከፍ ማለቱን አመልክቷል፡፡

ኢንተርኔትን መገደብ የአፍሪካን ኢኮኖሚ ጎትቷል
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:29 0:00

የIXP መለኪያ የተለያዩ በይነ መረቦች የተለያዩ ተጠቃሚዎችን ልውውጥ ወይም ትራፊክ የሚያስተናግዱበትን የሚያመላከት ሲሆን፣ ከአፍሪካ ስድስት አገሮች ከአንድ ነጥብ IXP በላይ ማስመዝገባቸው ተመልክቷል፡፡

የአብዛኞ የአፍሪካ አገሮች የኢንተርኔት ትራፊክ የጨመረው፣ ከአስርት ዓመታት በፊት፣ የልውውጥ መስመራቸውን ከአፍሪካ ውጭ ካሉ አገራት ጋር የዘረጉ በመሆኑ እንደሆነም አስታውቋል፡፡

መንግሥታዊ ድርጅት ያልሆነው ፣ የኢንተርኔት ማህበረሰብ፣ የአፍሪካ ቀጠና ምክትል ፕሬዚዳንት የሆኑት፣ ዳዊት በቀለ፣ የኢንተርኔት አጠቃቀምና ልማትን ለማጎልበት የሚሰሩ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት አፍሪካውያን የኢንተርኔት ተደራሽነትን እዚያው አፍሪካ ውስጥ ባሉት ተጠቃሚዎች መካከል በሚያደርጉት ልውውጥ እያሳደጉት ነው፡፡ እንዲህ ብለዋል ዳዊት

“አፍሪካ ውስጥ ያለውን የኢንተርኔት ልውውጥ በማሳደግ ከአፍሪካ ውጭ የሚደረገውን የኢንተርኔት ስምሪት ጉዞዎችን ብዛት ገድበናል፡፡ ይህንም በማድረግ የልውውጥ መስመሩ ወደ አፍሪካ እንዲመለስ ማድረግ እንችላለን፡፡ ይህ የአፍሪካ ተጠቃሚዎችን ተሞክሮ ለማሻሻል፣ የኢንተርኔቱን ፍጥነትና ቅልጥፍና ለማሳደግ እንዲሁም የግንኙነት ወጭ ለመቀነስ ይረዳል፡፡

መሠረቱን ዋሽንግተን ያደረገው ቡድን፣ የአፍሪካን የውስጥ ለውስጥ ልውውጥ በማሳደግ፣ 80 ከመቶ የሚሆነውን ትራፊክና ልውውጥ፣ በአህጉሪቱ ውስጥ እንዲሆን የማድረግ ግብ እንዳለው ይገልጻል፡፡

የኢንፍሮሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያው የሆኑት ማይክል ኒዬተጌካ እንደሚሉት፣ በህዝብ ዘንድ ያለው ፍላጎትና ጥያቄ የአፍሪካ መንግሥታት የኢንተርኔት አገልግልትን እንዲያሳድጉ እየገፋፋቸው ነው፡፡ እንዲህ ይላሉ ኒዬተጌካ

“ከወጣቱ ትውልድ መሸሽ አንችልም፡፡ ቁጥራቸው እጅግ በርካታ የሆኑ ወጣቶች አሉ፡፡ ለኢንተርኔትና ለዘመናዊ ቴክኖሎጂ ያላቸው ፍቅርና ተነሳሽነት ከወላጆቻችን እጅግ የላቀ ነው፡፡ ቴክኖሎጂን ከምንም ነገር በላይ መጠቀም ይቀናቸዋል፡፡ በመጨረሻም ሌላ የምጨመረው ነገር፣ በተለይ ለሞባይል ቴክኖሎጂ ደግሞ ያለው ፍቅር እጅግ ከፍተኛና ወሳኝ መሆኑን ነው፡፡ ትንሽ በዛ ያለ ቁጥር ያላቸው በአንጻራዊነት እጅግ ርካሽ የሆኑ የኢንተርኔት አገልግልትን ጨምረው ሊሰጡ የሚችሉ ስልኮች ገበያው ላይ አሉ፡፡ እነሱ ምን ያህል በከርካታ ሰዎች ኢንተርኔትን መጠቀም እንደሚችሉ የሚያሳዩና ትቅል ተጽእኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ ናቸው፡፡

እኤአ በ2020፣ International Foundation Corporation የተባለው ዓለም አቀፍ ተቋም ባደረገው ጥናት እንዳመለከተው፣ አፍሪካ፣ ኢንተርኔትን በመጠቀም ብቻ፣ ወደ ኢኮኖሚዋ 180 ቢሊዮን ዶላር ልታስገባ ትችላለች፡፡

ይሁን እንጂ ግን አንዳንድ መንግሥታት የዲጂታል ግንኙነትን ለመቆጣጠር ሲሉ፣ የማህበራዊ ትስስር ገጾችንና መድረኮችን እየዘጉ፣ በኢንተርኔት ተጠቃሚዎችም ላይ ከፍተኛ ቀረጥ እየጣሉ ነው፡፡

የኢንተርኔት ክፍያን በማመቻቸት የንግድ ዘርፍ ሥራ ላይ የተሰማራው የናይጄሪያው ኩባንያ የሲርቢት ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት፣ ኦሞኒዪ ኮላንዴ፣ ኢንተርኔትን ለመቆጣጠር የሚሰራ መንግሥት የንግዱን ዘርፍ ወደ ኋላ ይጎትተዋል በማለት የሚከተለውን ተናግረዋል፦

“ይህ ወደፊት ልንራምደ ሲገባን ወደኋላ የምንጎተትበት አካሄድ ነው፡፡ ማበረታት የነበረብን ተደራሽነትን፣ ሰዎች ለመፍትሄ የሚያደርጉትን ነጻ ግንኙነት ነው፡፡ በዚያ ላይ የንግድ ሰዎች ምርቶቻቸውን በበይነ መረቡ መስመር ላይ የሚያውሉ ከሆነ፣ እነዚያ መስመሮች በተዘጉ ወይም በተቋረጡ ቁጥር ገቢያ ባለመኖሩ ወደ እነዚያ መስመሮች የሚያደርሱ መንገዶችም አብረው ይቋረጣሉ፡፡ በበይነ መረቡ ላይ ገቢ የሚያገኙ ወገኖች ሊያገኙ የሚችሉት ነገር ባለመኖሩ በመስመሩ ላይ የሉም፡፡ በዚህ የተነሳ እኛም ትልቅ ገቢ እያጣን ነው፡፡”

በአፍሪካ የተባበሩት መንግስታት ኢኮኖሚክ ኮሚሽን እንደሚለው፣ በአፍሪካ የኢንተርኔት አገልግልት የሚያገኘው 20 ከመቶ የሚሆነው ህዝብ ብቻ ነው፡፡

የኢንተርኔት ማህብረሰብ አባላት ቡድንም፣ የአፍሪካ መንግስታት፣ የኢንተርኔት ተደራሽነትን፣ አብዛኛው ህዝብ ይኖርበታል ወደሚባለው ወደ ገጠር አካባቢዎች ለማዳረስ፣ የመሰረተ ልማቶችን እንዲያስፋፉ ግፊት እያደረጉ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

(የቪኦኤ ዘጋቢ፣ ሞሀመድ የሱፍ፣ ከናይሮቢ ከላከው ዘገባ የተወሰደ፡፡)

XS
SM
MD
LG