በአፍሪካ ምጣኔ ኃብት ላይ የተነጋገረው ዓለምአቀፍ ጉባዔ ተጠናቀቋል፡፡ በማቀናቀቂያው ላይ ታዲያ የአፍሪካ መሪዎች በሥራ ፈጠራ፣ በፍትሕና በተሻለ አስተዳደር መስኮች ተጨባጭ ውጤት እንዲያስገኙ ጥሪ ተላልፏል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቀድሞ ዋና ፀሐፊ ኮፊ አናን መሪዎቹ የየዜጎቻቸውን ሕይወት ለማሻሻል እንዲሠሩ በማሳሰብ “ሙሉ የሕሊና ኃይላቸው በሚያስችላቸው መጠን ግፊት ለማሣደር የሞከሩበትን ንግግር አድርገዋል” ይላል ጉባዔው ከተካሄደባት አዲስ አበባ የተጠናቀረው ዘገባ፡፡
ኮፊ አናን በሰባ አራት ዓመታቸው ኃይለኛ ሆኑ - ብሎ ይጀምራል የፒተር ሃይንላይን ዘገባ፡፡ የመንግሥታቱ ድርጅት መሪነታቸውን ካስረከቡ ከስድስት ዓመታት በኋላ የጋናዊው የሥርዓተ-መንግሥት ሰው የኮፊ አናን የፖለቲካና የቢዝነስ መሪዎች በተሣተፉበት በዚህ ጉባዔ ላይ መገኘት ጎልቶ ታይቷል፡፡ ስሙን ለአፍሪካ ችግር ከመድረስ ጋር ያስተሣሰረው እንግሊዛዊው የሙዚቃ ሰው ባብ ጌልዶፍም እዚያው ነበር፡፡
ኮፊ አናን በአፍሪካ ዕድገት ላይ የተጠናቀረ ሪፖርት አቅርበዋል፡፡ “ቀልብ ሣቢ” ያሉት የአሕጉሪቱ የዛሬ የምጣኔ ኃብት ዕድገት በቂ የሥራ ዕድሎች ሣይፈጠሩ ወይም የተሻለ ሕይወት ተስፋ ሣይጨበጥ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወጣት አፍሪካዊያን ለሥራ ብቁ ወደሚሆኑበት ዕድሜ መድረሣቸው ዕድገቱን አደጋ ላይ እንደሚጥለው አሳስበዋል፡፡
“የአፍሪቃ ፖለቲካ ሂደት በቋፍ ያለና ወደኋላ ተንሸራትቶ ወደ ቀድሞዎቹ የወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ሁኔታዎች የመመለስ ሥጋት የተጋረጠበት ነው” ብለዋል አናን።
በአፍሪቃው የምጣኔ ኃብት ጉባዔ በርካታ መድረኮች ላይ የአህጉሪቱን ሴቶች ውሳኔ ሰጭ እንዲሆኑ ማስቻል ተወስቷል።
“አንድ ለአፍሪቃ ቅድሚያ ሊኖረዉ ይገባል ብዬ የምለዉ፥ ትምህርት ነው” ብለዋል ሚስተር ኮፊ አናን። በ1 ቢሊዮን ከሚገመተው ሕዝቧ 60 ከመቶው ዕድሜው ከ30 ዓመት በታች ወጣት በሆነባት አህጉር ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገትና የፖለቲካ መረጋጋት እንዲኖር ለሥራ ፈጠራ የሚያበቃ ትምህርት አስፈላጊነት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ “ወደ ሥልጣን ሲወጡ ይዘው የተነሡት አጀንዳ ምንም ያህል የተቀደሰ ይሁን የአፍሪካ መሪዎችን ወደ ሙስና የምትስባቸው መርዝ ምን ትሆን?” ይህ አዲስ አበባ ላይ በአፍሪካ ምጣኔ ኃብት ላይ በተነጋገረው ዓለምአቀፍ ጉባዔ ላይ እንዲሁ የተባለ ጥያቄ ነው፡፡
በዚህ ስብሰባ ላይ የአፍሪካ ሃገሮች መሪዎችም ተገኝተዋል፡፡
ለተጨማሪና ዝርዝር ዘገባዎችን ያድምጡ፡፡