የአፍጋኒስታኑ አክራሪ እስላማዊ ገዥዎች በዩናይትድ ስቴትስ የታገደውን 7 ቢሊዮን ዶላር የአፍጋንስታን መንግሥት ገንዘብ የፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ሙሉውን ለመልቀቅ ፈቃደኛ ካልሆነ ዋሽንግተንን አስመልክቶ የሚያራምዱትን ፖሊሲ ዳግም ለማጤን ማቀዳቸውን ተናገሩ።
ፕሬዚዳንት ባይደን ባለፈው አርብ ነው፣ ከዩናይትድ ስቴትስ ባንኮች ውስጥ እንዳይንቀስቀስ ተደርጎ ከቆየው 7 ቢሊዮን ዶላር ከፊሉን ለአፍጋኒስታን የሰብአዊ እርዳታ እንዲውል ሲሉ ፕሬዚዳንታዊ ትዕዛዝ ያስተላለፉት። በዚያው ትዕዛዛቸውም ቀሪው 3.5 ቢሊዮን ዶላር በዋሽንግተን ዲሲ እና በኒው ዮርክ በአሸባሪዎች የተፈጸሙት የመስከረም አሥራ አንዱ ጥቃቶች ሰለባ የሆኑ ቤተሰቦች ላቀረቧቸው እና በመታየት ላሉት ክሶች ክፍያ ይውል ዘንድ ተይዞ እንዲቆይ ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የታሊባን ቃል አቀባይ ትናንት ሰኞ ባወጣው መግለጫ የመስከረም አሥራ አንዱ የአሸባሪዎች ጥቃቶች “ከአፍጋኒስታን ጋር ምንም ግንኙነት የላቸውም።” ሲሉ ተችተዋል።
ቃል አቀባዩ አክለውም ዩናይትድ ስቴትስ አቋሟን የማትቀይር እና “ቆስቋሽ” ባሉት ተግባሯ የምትቀጥል ከሆነ እስላማዊዋ ኢሚሬትም ዩናይትድ ስቴትስን አስመልክቶ የምታራምደውን ፖሊሲ እንደገና ለማጤን ትገደዳለች” ሲሉ የአፍጋኒስታንን የኦፊሴል መጠሪያ በመጥቀስ ዕቅዳቸውን ተናግረዋል።
የመስከረም አስራ አንዱ የአሸባሪዎች ጥቃት በተፈጸመበት ወቅት አፍጋኒስታንን ይመራ የነበረው ታሊባን፤ ለአልቃይዳው መሪ እና የጥቃቱ አውጠንጣኝ ኦሳማ ቢንላደን መሸሸጊያ በመስጠት ይወነጀላል። ታሊባን በጊዜው ቢንላደን ተላልፎ እንደሰጣት ዋሽንግተን ያቀረበችውን ጥያቄ ውድቅ ካደረገ በኋላ በነበሩ ጥቂት ሳምንታት ውስጥ በዩናይትድ ስቴትስ መሩ ዓለም አቀፍ ዘመቻ ከስልጣን መወገዱ ይታወሳል።
በሌላ በኩል ዩናይትድ ስቴትስ ባለፈው ነሃሴ ወር አፍጋኒስታን ለቃ በወጣችበት ወቅት ሃያ ዓመታት የተጠጋው ጦርነት ቢያበቃም፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና ሌሎች ዓለም አቀፍ የረድኤት ቡድኖች እንደሚሉት ግን፤ አፍጋኒስታን ካለፉት አራት አስርት ዓመታት በላይ በዘለቁ ግጭቶች እና የተፈጥሮ አደጋዎች ከታዩት በዓለም እጅግ የከፉ ከሚባሉት የሰብዓዊ ቀውሶች አንዱ ይጠብቃታል። .
ከአገሪቱ ህዝብ ከግማሽ በላይ ከሚሆነው እና እጅግ በበረታ ድህነት ውስጥ ከሚገኘው ቁጥሩ ሃያ አራት ሚሊዮን እንደሚደርስ የሚገመት አፍጋናዊ ለከፋ የምግብ እጥረት የተጋለጠ ሲሆን፤ በያዝነው የአውሮፓውያኑ 2022 መጨረሻ ቁጥራቸው አንድ ሚሊዮን የሚደርስ ዕድሜያቸው ከአምስት አመት በታች የሆኑ ህጻናትም በረሃብ ሳቢያ ለህልፈት ሊዳረጉ እንደሚችሉ የመንግሥታቱ ድርጅት ገልጿል።