በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የባሕር ዘለሉን ጉዲፈቻ መጠን የሚቀንስ መመሪያ ወጣ


ኢትዮጵያ በማጭበርበርና በሙስና ተውጧል የሚባለውን የጉዲፈቻ አሠራር ለማፅዳት በሚል በከፈተችው ዘመቻ ከባሕር ተሻጋሪው ጉዲፈቻ ዘጠና ከመቶ የሚሆነውን ለመቁረጥ መወሰኗ ተዘግቧል፡፡

እርምጃው ወላጆቻቸውን ያጡ ሕፃናት በውጭ አሣዳጊ ቤተሰብ የማግኘታቸውን እንደመጨረሻ አማራጭ የሚታይ ምርጫ ይጎዳዋል ሲሉ የጉዲፈቻ ድርጅቶችና የሕፃናት ደሕንነት ተሟጋቾች እንደሚሰጉ አዲስ አበባ የሚገኘው ሪፖርተራችን ፒተር ሃይንላይን ዘግቧል፡፡

ከፊታችን መጋቢት 1 ቀን ጀምሮ በቀን የሚያስተናግደው አምስት የባሕር ዘለል ጉዲፈቻ ማመልከቻዎችን ብቻ እንደሚሆን የኢትዮጵያ የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

እስከአሁን መሥሪያ ቤቱ የሚያስተናግደው በቀን ሃምሣ የሚደርሱ የጉዲፈቻ ማመልከቻዎችን መሆኑንና ከእነዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሕፃናት የሚወሰዱት በአሜሪካዊያን ቤተሰቦች መሆኑ ታውቋል፡፡

በቀን የሚስተናገዱት ማመልከቻዎች ቁጥር ወደ አምስት መውረዱ ሕፃናቱ በእርግጥ ወላጆቻቸውን ያጡ ለመሆናቸው ጥልቅ ፍተሻ ለማድረግ በቂ ጊዜ እንደሚሰጥ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ያወጣው ትዕዛዝ ይጠቁማል፡፡

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አብይ ኤፍሬም እንደሚሉት መሥሪያ ቤታቸው እርምጃውን እንዲወስድ ያስገደደው እጅግ የተስፋፋ ያሉትን ማጭበርበር የሚጠቁሙ ሪፖርቶች በየጊዜው መድረሣቸው ነው፡፡

በጉዳዩ ላይ የተካሄዱ ምርመራዎች አንዳንድ ጨዋነት የጎደላቸው የጉዲፈቻ አስፈፃሚዎች ወላጆች በተጭበረበረ መንገድ ልጆቻቸውን እንዲሰጡ ካደረጉ በኋላ ከባሕር ዘለል ጉዲፈቻ ከሚገኘው እጅግ የበዛ ገንዘብ በርከት ያለውን እንደሚወስዱ የሚያሣዩ ማስረጃዎች መያዛቸውንም ዘገባው ይጠቁማል፡፡

አንድ አሜሪካዊ ቤተሰብ አንድ ኢትዮጵያዊ ሕፃን ወስዶ ለማሣደግ ከሃያ ሺህ ዶላር በላይ እንደሚከፍል ይታወቃል፡፡

ባለፈው የአውሮፓዊያን ዓመት ብቻ ከ2500 በላይ ኢትዮጵያዊያን ሕፃናት ወደ ዩናይትድ ስቴትስ በጉዲፈቻ መግባታቸውን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ሰነዶች ያሣያሉ፡፡ ይህ ቁጥር በቅርብ ካለፉ ዓመታት ጋር ሲነፃፀር ከአሥር እጅ በላይ የተመነደገ ሲሆን ይህም ኢትዮጵያን ሕፃናትን ለማሣደግ የሚጓዙ አሜሪካዊያን በዓለም ሁለተኛ መድረሻ ያደርጋታል፡፡ አንደኛዋ ቻይና ነች፡፡

የሕፃናት ደሕንነት ተሟጋች ባለሙያዎች ተበላሽቷል የሚባለውን አሠራር የማፅዳቱን ሃሣብ በጥቅሉ ይደግፉታል፡፡

አንድ እርምጃውን “አስገራሚ” ያሉ የጉዲፈቻ ድርጅት ወኪል ስማቸው እንዳይጠራ ጠይቀው በሰጡት አስተያየት፣ “በቀል ነው” ይሉታል፡፡ በቀሉ ምንድነው፤ ይህንን የጉዲፈቻ ጉዳይ መንግሥት የያዘው “በግድ የለሽነት በንዝህላልነት ነው” የሚል ትችት በቅርቡ በመሰማቱ “ያ ያበሣጨው መንግሥት የወሰደው እርምጃ ነው” ባይ ናቸው፡፡

ቅነሣው ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የሚወሰዱትን ሕፃናት ቁጥር ካለፈው ዓመት 2500 በዚህ ዓመት ወደ አምስት መቶ ሊያወርደው እንደሚችል የአዲስ አበባው የአሜሪካ ኤምባሲ ኮንሱላር ክፍል ኃላፊ አቢጌል ራፕ አመልክተዋል፡፡

“አሁን ትልቁ ችግር - ይላሉ ሚስ ራፕ - ጉዳያቸው የተጀመረና በእንጥልጥል ያለ አንድ ሺህ የሚሆኑ ሕፃናትና ጠያቂ አሣዳጊዎቻቸው ጉዳይ ነው፡፡ እንዲታይላቸው ከአንድ ዓመት በላይ መጠበቅ ሊገደዱ ነው ማለት ነው፡፡”

የጉዲፈቻ አስፈፃሚ ድርጅቶች አዲሱን መመሪያ እንደመነሻ ሊወስዱት እንደሚገባ፤ ይህ ደግሞ ወላጆቻቸውን ያጡ ሕፃናት በሚገኙባቸው ድርጅቶች ውስጥ የገቡ ሕፃናት እንዴት ወደዚያ ሊመጡ እንደቻሉ ማወቅን እንደሚጨምር የኮንሱላር ክፍሉ ኃላፊ አቢጌል ራፕ አሣስበዋል፡፡

የሕፃናት ንግድ” ተብሎ በውጭ በተሰየመ ሥራ ላይ ተሠማርተዋል የተባሉትን ለማፅዳት በሚወስደው እርምጃ መንግሥት አርባ አምስት የሚሆኑ ማሣደጊያዎችን እንደሚዘጋ ባለሥልጣናቱ የጠቆሙ መሆኑን ራፕ ገለፀዋል፡፡

“በሥርዓቱ ውስጥ ያሉ የተበላሹ አሠራሮችን ነቅሎ ለመጣልና አምስት ሚሊየን የሚሆኑት ወላጆቻቸውን ማጣታቸው በትክክል ለሚታወቅ ኢትዮጵያዊያን ሃገር በቀል መፍትሔ ለመሻት አዲሱ መመሪያ ጠቃሚ እርምጃ ነው፤” ብለውታል አዲስ አበባ የሚገኘው የመንግሥታቱ ድርጅት የሕፃናት ፈንድ (ዩኒሴፍ) ኃላፊ ቴድ ቻይባን፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በዚያ ከሚንቀሣቀሱት ሃያ ሁለት የዩናይትድ ስቴትስ የጉዲፈቻ አስፈፃሚ ድርጅቶች የአንዱን ፈቃድ ባለፈው ወር ነጥቋል፡፡ ዋና መሥሪያ ቤቱ ሚኔሶታ የሚገኘውን “በተር ፊውቸር አዶፕሽን ሰርቪስስ” የተባለውን ድርጅት ፍቃድ ለመነጠቅ ያበቃው ወላጆቻቸው በሕይወት ያሉ ሕፃናትን ወላጆቻቸውን በሕይወት ያጡ አስመስሎ ሰነዶችን ማቅረቡ መሆኑ ተነግሯል፡፡ ይሁን እንጂ ድርጅቱ ክሱን አይቀበልም፤ ፍቃዱ መሠረዙንም “አግባብ አይደለም” ብሎ እየተሟገተ ነው፡፡

የዚህ ዘገባ አጠናቃሪ ፒተር ሃይንላይን ከትናንት በስተያ ዐርብ ሚኔሶታ ወደሚገኘው የድርጅቱ የአሜሪካ ቢሮ ደውሎ ነበር፡፡ መልስ እንዳላገኘ ፅፏል፡፡ ለማንኛውም ጥረታችን ይቀጥላል፡፡

ለማንኛውም ከበተር ፊውቸር ጋር ውል የገቡ ወይም ጉዳይ የጀመሩ ቤተሰቦች የሕግ ባለሙያዎችን እንዲያማክሩ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በዌብ ሣይቱ ላይ አሣስቧል፡፡

ዘገባውን ያዳምጡ፡፡

XS
SM
MD
LG