የመቀሌ ሕዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተለየ ችግር የለውም ሲሉ በግንቦት 16ቱ የፓርላማ ምርጫ መቀሌ ውስጥ ሕወሓት/ኢሕአዴግን ወክለው የሚወዳደሩት ዶ/ር አዲስዓለም ባሌማ ለቪኦኤ በሰጡት ቃለምልልስ ተናግረዋል፡፡
“ችግሩ ተመሣሣይ ነው፤ ከድኅነት መውጣት፡፡ ኢኮኖሚው ማደግ አለበት፤ በመቀሌም ቢሆን በተመሣሣይ መንገድ ኢኮኖሚው እንዲያድግ እናደርጋለን” ብለዋል የሕወሓቱ የመቀሌ ዕጩ ተወዳዳሪ፡፡
መቀሌን የውኃ ችግር ብዙ ጊዜ የሚፈታተናት መሆኑን የገለፁት ዶ/ር አዲስዓለም በአሁኑ ጊዜ የተለያዩ የማስተንፈሻ ፕሮጀክቶች እየተሠሩ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡
ይሁን እንጂ ለችግሩ ዘላቂ መፈትሔ ለመስጠት የሚያስችል ግድብ ለመሥራት ዕቅድ ተይዞ ዕቅዱ በፌደራል መንግሥቱ ተቀባይነት ማግኘቱንና ከቻይናው ኤክሲም ባንክ ብድር ተጠይቆ ምላሽ እየተጠበቀ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
መቀሌ የኢንዱስትሪ ማዕከል መሆኗንና የጨርቃጨርቅና የብረታብረት ፋብሪካዎች ወደመቀሌ እየገቡ መሆናቸውንም አዲስዓለም አመልክተዋል፡፡
የመልካም አስተዳደር ጉድለቶች እንዳሉ የጠቆሙት ዶ/ር አዲስዓለም “ከሕዝቡ ጋር እየተመካከርን እንፈታቸዋለን” ብለዋል፡፡
“በአንድ በኩል ግልፅነትን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ተጠያቂነትን እያጠናከርን እንሄዳለን” ብለዋል ዶ/ር አዲስዓለም ባሌማ፡፡
ለዝርዝሩ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡