በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በመስጂዶች ማፍረስ በቀጠለው ተቃውሞ የሦስት ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተገለጸ


በመስጂዶች ማፍረስ በቀጠለው ተቃውሞ የሦስት ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተገለጸ
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:22 0:00

በኦሮሚያ ክልል የሸገር ከተማ አስተዳደር የተፈጸመውን የመስጂዶች ማፍረስን በማውገዝ፣ በዛሬ ዐርብ፣ የጁመዓ ሶላት ሥነ ሥርዐት መጠናቀቅ በኋላ፣ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በቀጠለው ተቃውሞ፣ በጸጥታ ኀይሎች በተወሰደ ርምጃ፣ የሞት እና የአካል ጉዳት መድረሱ ተገለጸ፡፡

በታላቁ አንዋር መስጂድ እና አካባቢው በነበረው ክሥተት፣ የሰው ሕይወት ማለፉንና በርካቶች መጎዳታቸውን፣ አንድ እማኝ ለአሜሪካ ድምፅ ገልጿል፡፡ ከማለዳ ጀምሮ በአካባቢው ከነበሩ የጸጥታ ኃይሎች ተኩስ መሰማት እንደጀመረ፣ ከመስጂዱ የአደጋ ጊዜ የአዛን መልዕክት መተላለፉን ተከትሎ፣ በሌሎች መስጂዶችም የተቃውሞ እንቅስቃሴ መደረጉን እማኙ አብራርቷል፡፡

የመንግሥት የጸጥታ እና የደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል በበኩሉ፣ ዛሬ ምሽት ባወጣው መግለጫ፣ በታላቁ አንዋር“ረብሻ” ሲል በጠራው ተቃውሞ በተፈጠረ ግጭት፣ የሦስት ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ፣ የተወሰኑ ሰዎችን ጨምሮ ለጸጥታ ሥራ በተሠማሩ 63 የፖሊስ አመራር እና አባላት ላይ ቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን አስታውቋል፡፡ በንብረት ላይም እስከ አሁን ግምቱ ያልተወቀ ኪሳራ እንደ ደረሰ ጠቁሟል፡፡

ችግሩ የተከሠተው በታላቁ አንዋር መስጅድ፣ የጁምዓ ሶላት በሰላም ተጠናቅቆ ሕዝብ ሙስሊሙ እየተመለሰ ባለበት ኹኔታ መኾኑንም አመልክቷል፡፡አክሎም፣“ፀረ ሰላም ኃይሎች” ሲል የገለጻቸው አካላት፣ “የእምነቱ ተከታዮች በሕጋዊ መንገድ ያቀረቡትን ጥያቄ ጠልፈው የራሳቸውን እኩይ ዓላማ ለማሳካት፣ ረብሻውን ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለማዛመት ያደረጉትን ጥረት፥ የጸጥታ ኃይሉ፣ ሕዝበ ሙስሊሙ እና የሃይማኖቱ አባቶች በጋራ በአደረጉት ርብርብ መቆጣጠር ተችሏል፤” ብሏል፡፡

ኾኖም፣ ለአሜሪካ ድምፅ አስተያየቱን የሰጠ አንድ እማኝ፣ በአንዋር መስጂድ ተፈጥሮ ከነበረው የተቃውሞ እንቅስቃሴ እና የፖሊስ የኃይል ርምጃ በኋላ፣ ከመስጂዱ የአደጋ ጊዜ የአዛን መልዕክት መተላለፉን ተከትሎ፣ በሌሎች መስጂዶችም የተቃውሞ እንቅስቃሴ መደረጉን አብራርቷል፡፡

ዛሬ የተቃውሞ ድምፅ የተሰማው፣ በመስጂዶች ፈረሳ ጉዳይ ላይ፣ ከመንግሥት ጋራ እየተነጋገረ እንደኾነ ጠቅሶ፣ ሕዝበ ሙስሊሙም፥ ከተቃውሞ እንቅስቃሴ በመታቀብ ውጤቱን እንዲጠባበቅ፣ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በጠየቀ ማግሥት ነው፡፡

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ፣ በደረሰው ጉዳት ማዘኑን አስታውቋል፡፡በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ አስተዳደር ውስጥ፣ የተፈጸመውን የመስጂዶች ፈረሳ በማውገዝ፣ በዐዲስ አበባ፣ የእምነቱ ተከታዮች የተቃውሞ ድምፅ ሲያሰሙ፣ የዛሬው ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡

ባለፈው ዓርብ፣ ግንቦት 18 ቀን 2015 ዓ.ም. ከሶላት በኋላ፣ በአንዋር መስጂድ፣ የተቃውሞ ድምፅ መሰማቱንና ፖሊስ በወሰደው ርምጃ የሁለት ሰዎች ሕይወት እንዳለፈ መገለጹ ይታወቃል፡፡

በተያያዘ ዜና፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ባለፈው ሳምንት በነበረው ተቃውሞ፣ የሁለት ሰዎች ሕይወት ማለፉን እንዳረጋገጠ ገልጾ፣ የጸጥታ ኃይሎች ያልተመጣጠነ የኃይል ርምጃ ከመውሰድ እንዲቆጠቡ ጠይቋል፡፡

XS
SM
MD
LG