በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በየመን ባህር ዳርቻ በሰጠመ የፍልሰተኞች ጀልባ 49 ሲሞቱ 140 የደረሱበት አልታወቀም


የመን ካርታ
የመን ካርታ

በየመን የባህር ዳርቻ ፍልሰተኞችን አሳፍራ ስትጓዝ የነበረች ጀልባ በመስጠሟ በትንሹ 49 ሰዎች ሲሞቱ 140 ያህሉ የደረሱበት አለመታወቁን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት (አይኦኤም) አስታወቀ።

ከሶማሊያ ሰሜናዊ የባህር ዳርቻ ተነስታ ሰኞ እለት በየመን ደቡባዊ የባህር ዳርቻ የሰጠመችው ጀልባ፣ ወደ 260 የሚጠጉ ሶማሊያውያንን እና ኢትዮጵያውያንን አሳፍራ ስትጓዝ እንደነበር የፍልሰት ድርጅቱ ጨምሮ ገልጿል።

ኤጀንሲው እንዳስታወቀው ማክሰኞ እለትም የማፈላለግ ጥረቱ እንደቀጠለ ሲሆን እስካሁን 71 ሰዎችን ማትረፍ ተችሏል። ህይወታቸውን ካጡት ሰዎች መካከል 31 ሴቶች እና 6 ልጆች ይገኙበታል።

የመን ስራ ፍለጋ ከምስራቅ አፍሪካ እና ከአፍሪካ ቀንድ ተነስተው ወደ ባህረ ሰላጤው ሀገራት ለመጓዝ የሚሞክሩ ፍልሰተኞች ዋና መተላለፊያ መንገድ ነች። ላለፉት አስር አመታት በየመን የእርስ በእርስ ጦርነት እየተካሄደ ቢሆንም፣ እ.አ.አ ከ2021 እስከ 2023 ባለው ጊዜ ወደ ሀገሪቱ የሚገቡት ፍልሰተኞች ቁጥር በሦስት እጥፍ አድጎ ከ27 ሺህ ወደ 90 ሺህ ከፍ ማለቱን አይኦኤም ባለፈው ወር አስታውቆ ነበር። በአሁኑ ወቅት የፍልሰተኞቹ ቁጥር 380 ሺህ መድረሱን የተቋሙ መረጃ ያሳያል።

ህገወጥ አዘዋዋሪዎቹ ፍልሰተኞቹን የመን ለማድረስ እጅግ በተጨናነቁ እና አደገኛ በሆኑ ጀልባዎች የቀይ ባህርን ወይም የኤደን ባህረ ሰላጤን እንዲያቋርጡ ያደርጓቸዋል። በሚያዚያ ወር በተመሳሳይ ሁኔታ ወደ የመን ለመጓዝ የሞከሩ ሰዎች ጀልባቸው በጅቡቲ የባህር ዳርቻ ላይ ተገልብጦ በትንሹ የ62 ሰዎች ህይወት አልፏል።

አይኦኤም የሰጠሙትን 480 ሰዎች ጨምሮ፣ ቢያንስ 1ሺህ 860 ሰዎች ህይወታቸው ማለፉን ወይም የደረሱበት እንደማይታወቅ አመልክቷል።

ሰኞ እለት የደረሰው የጀልባ መስመጥ አደጋ፣ ከፍልሰት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት እና ፍልሰተኞች በመንገዳቸው ላይ ደህንነታቸው የተጠበቀ መሆኑን እንድናረጋግጥ ተባብሮ መስራት አስፈላጊ መሆኑን እንድናስታውስ የሚያደርግ ነው ሲሉ የአይኦኤም ቃል አቀባይ ሞሃመዳሊ አቡንጄላ ተናግረዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG