በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የፍልስጤም አስተዳደር ፕሬዝደንት ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር በአዲስ አበባ ተነጋገሩ


የፍልስጤሙ አስተዳደር ፕሬዝደንት ማህሙድ አባስ ለሶስት ቀናት የስራ ጉብኝት አዲስ አበባ የገቡት በትናንትናው እለት ነበር። በመካከለኛው ምስራቅ የሰላም ጥረት ድርድሩ ተቋርጦ፤ በሶስተኛ ወገን ለዚያውም ለየብቻቸው የእስራኤልና የፍልስጤም ባለስልጣናት በእጅ-አዙር በመነጋገር ባሉበት ወቅት ነው፤ ማህሙድ አባስ ወደ አዲስ አበባ ያመሩት።

ሚስተር አባስ ከኢትዮጵያና ከአፍሪካ ህብረት ባለስልጣናት ጋር ውይይት ሲያደርጉ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ናታንያሁ በዋሽንግተን ዲሲ ከዩናይትድ ስቴይትሱ ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ጋር የሰላም ስምምነቱን ለማስቀጠል በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ በመማከር ላይ ነበሩ።

ከኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር ከተዋያዩ በኋላ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት ማህሙድ አባስ የፍልስጤም አስተዳደር ከእስራኤል ጋር የሰላም ውይይት ለመጀመር እንደሚፈልግና እስካሁን ከእየሩሳሌም የተገኘ ምላሽ አለመኖሩን ተናግረዋል።

አባስ በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ወቅት በዝርዝር ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊና ከአፍሪካ ህብረት ባለስልጣናት ጋር ስላደረጉት ውይይት የተናገሩት የለም። በጥቅሉ 1.5 ሚሊዮን ፍልስጤማዊያን መሰረታዊ አቅርቦቶች እንዳያገኙ ያግዳል ያሉትን እስራኤል በጋዛ ላይ የጣለችው የአቅርቦት እንቅስቃሴ እገዳ እንዲነሳና፤ ተጨማሪ የአይሁድ ሰፈራዎች እንዳይኖሩ ጠይቀዋል።

በመካከለኛው ምስራቅ ታሪክ 7 መጻህፍቶችን ለንባብ ያበቁት የታሪክ ምሁር ሀጋር ኢርሊክ ኢትዮጵያ ከታሪክና ከቅርበት አንጻር ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ጥቅሞች አሏት ይላሉ።

“ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት ዋና ጽህፈት መዲና ናት። ስለዚህ ለቀሪው አህጉር መከፈት የዲፕሎማሲ ቁልፉ በአዲስ አበባ ነው ያለው። እንዳልከው በተባበሩት መንግስታት ድርጅት 53 ድምጽ ማግኘት ማለት ነው። እነዚህ ድምጾች ለአረብ-እስራኤል ግጭት ወሳኝ ናቸው። ስለዚህ ከኢትዮጵያና ከአፍሪካ ጋር ግንኙንት ለመመስረት መሞከራቸው ስሜት የሚሰጥ ነው። ኢትዮጵያ ለፍልስጤማዊያን ጠቃሚ የመሆኗን ያህል ፍልስጤምም ለኢትዮጵያ ትጠቅማታለች፣” ብለዋል።

ከ1960ቹ መጨረሻ ጀምሮ ፍልስጤማዊያኑ በአዲስ አበባ የቆንስላ ግንኙነት መስርተዋል። የአረብ ሊግም ባለፈው አመት በኢትዮጵያዋ መዲና ቢሮ ከፍቷል። ይሄ እያደገ የመጣው የዲፕሎማሲ ግንኙነት በሁለቱም በኩል ጠቃሚ መሳሪያ እንደሆነ ፕሮፌሰር ኢርሊክ ይናገራሉ።

በአፍሪካ ቀንድ በርካታ የእስልምና አክራሪ አንጃዎች ሲፈጠሩ ይታያሉ። እነዚህ አንጃዎች ደግሞ ከበርካታ የውጭ ሀይሎች ድጋፍ ያገኛሉ። ለምሳሌ በሶማሊያ የሚንቀሳቀሰውና ኢትዮጵያን ጨምሮ ለአካባቢው አገሮች የደህንነት ስጋት የሆነው አል-ሸባብ ከፍልስጤም አክራሪ የእስልምና ቡድኑ ኻማስ ድጋፍ ያገኛል። ይህንን ለማስቆም የአፍሪካ መሪዎች በተለይ የአፍሪካ ቀንድ ከለዘብተኛ ፍልስጤማዊያን ጋር መስራት ይፈልጋሉ።

በአንድ ጎን ለዘብተኛው የማህሙድ አባስ መንግስት አፍሪካን በዚህ ረገድ ሲጠቅም፤ የፍልስጤም አስተዳደር ደግሞ በአለም አቀፍ ደረጃ እውቅናን ለማግኘት፤ እንዲሁም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት መድረኮች የአፍሪካን ድጋፍ በመሻት ግንኙነቱን በማጠናከር ላይ ያለው።

ሚስተር ኢርሊክ እንደሚሉት ኢትዮጵያ ምንም እንኳን በርካታ ክርስቲያኖች የሚኖሩባት አገር ብትሆንም፤ ሰፊ ቁጥር ያላቸው ሙስሊሞችም በዚያው ይኖራሉ። በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያ ለዘብተኛ ከሆኑ የአረብ አጋሮቿ ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖራት ትፈልጋለች። በመካከለኛው ምስራቅ ችግር ሲኖር የአፍሪካ ቀንድ ትታወካለች፤ በበተገላቢጦሹም “አፍንጫ ሲነካ..አይን ያለቅሳል ለካ..” አይነት እውነት ነው ይላሉ ለአስርት አመታት የኢትዮጵያና የመካከለኛው ምስራቅ ታሪክን ያስተማሩትና መጻህፍት ያሳተሙት ሀጋይ ኢርሊክ። በባህልና ሀይማኖትም ቢሆን የወደፊት ግንኙነቶች ሊጎለብቱ እንደሚገባቸውም ያሳስባሉ።

የፍልስጤሙ ፕሬዝደንት ማህሙድ አባስ ለተጨማሪ አንድ ቀን በአዲስ አበባ ይቆያሉ። በዚህ የስራ ጉብኝት የአፍሪካን ድጋፍ በተባበሩት መንግስታትና በተለያዩ አለም አቀፍ መድረኮች ለማግኘት ሚስተር አባስ ከአፍሪካ ህብረት ባለስልጣናት ጋር ይነጋገራሉ።

XS
SM
MD
LG