የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፋታህ ኤል-ሲሲ የሦስት ቀናት ጉብኝት ለማድረግ አዲስ አበባ እንደሚገቡ ተገልጿል፡፡
የሱዳኑ የኢንተርኔት ጋዜጣ ሱዳን ትሪብዩን ካይሮ-ግብፅ የሚገኘውን አል-ማስሪ አል-ዩም ጋዜጣን ጠቅሶ እንደዘገበው የግብፁ መሪ በዚሁ ጉብኝታቸው ወቅት የታላቁ ኅዳሴ ግድብ ግንባታን በሚመለከተው የስምምነት ማዕቀፍ ውስጥ አለመግባባት ባለባቸው የስምምነት ነጥቦች ላይ መፍትሔ ለመፈለግ ነው፡፡
በዚያ ስምምነት ሠነድ ውስጥ ግብፅ እንዲገቡ የምትፈልጋቸው ቁልፍ የሚባሉ ነጥቦች (እንደ ማሻሻያ ወይም ለውጥም የታሰቡ ናቸው) ግብፅ በናይል ውኃዎች ላይ “ያላትን ታሪካዊ መብት” ማረጋገጥና ወደ ኅዳሴ ግድብ ግንባታ የሚገባው የውኃ መጠን “እንዲቀንስ ማድረግ” የሚሉ ይገኙበታል፡፡
ሰነዱን ፕሬዚዳንት ኤል-ሲሲ ለኢትዮጵያው ጉብኝታቸው አዲስ አበባ በሚገቡበት በሚገቡበት ዕለት የፊታችን ሰኞ፣ መጋቢት 14/2007 ዓ.ም ሱዳን ዋና ከተማ ኻርቱም ላይ ይፈረማል ተብሏል፡፡
የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ሃሰን ኦማር አል-በሺር ለኢትዮጵያና ለግብፅ መሪዎች ያቀረቡላቸውን ግብዣ ሁለቱም ተቀብለዋል ተብሎ ተዘግቧል፡፡
ለቪኦኤ ማብራሪያ የሰጡት የኢትዮጵያ የውኃ፣ ኢነርጂና መስኖ ሚኒስትር አቶ ዓለማየሁ ተገኑ የተዘጋጀው ስምምነት “ታሪካዊ መብት” ወይም “የውኃ መጠን” ወይም “የግድብ ቁመት መቀነስ” እና የመሳሰሉ ሃሣቦች የሌሉበት መሆኑንና “ሊኖሩበትም እንደማይገባ” ጠቁመው ኢትዮጵያ ለመፈረም ዝግጁ መሆኗን አመልክተዋል፡፡
ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡