በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የረሃብ ቀውስ በምሥራቅ አፍሪካ እንዳስፈራ ነው


ፎቶ ፋይል፦ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በድርቁ ምክንያት የተጎዱ ከብቶች
ፎቶ ፋይል፦ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በድርቁ ምክንያት የተጎዱ ከብቶች

በኢትዮጵያ፣ በኬንያና በሶማሊያ ስፋት ያለው አካባቢ ለአራት ተከታታይ ዓመታት ዝናብ ባለመጣሉ የበረታ የረሃብ አደጋ እንዳንዣበበ መሆኑን የዓለም ምግብ ፕሮግራም በድጋሚ አስጠነቀቀ።

ባለፉት አርባ ዓመታት ውስጥ አልታየም በተባለው በዚህ የአየር ንብረት መዛባትና የተራዘመ ድርቅ ምክንያት ሶማሊያ፣ ደቡብና ደቡብ-ምሥራቅ ኢትዮጵያ እንዲሁም ምሥራቅ ኬንያ ውስጥ ብዙ ሰው መፈናቀሉንና በሚሊዮኖች የሚቆጠር ከብት ማለቁን የረድኤት ድርጅቶች ጠቁመዋል።

ሰባት ሚሊዮን የሚሆኑ ህፃናት ባለው ችግር ምክንያት በቂ ምግብ ስለማያገኙ በብርቱ ረሃብ መጎሳቆላቸውን የተባበሩት መንግሥታት የህፃናት አፋጣኝ ድጋፍ ፈንድ /ዩኒሴፍ/ አስታውቋል።

በሌላ በኩል በአሁኑ የዝናብ ወቅት በአንዳንድ አካባቢዎች እየጣለ ያለው ዶፍ ያስከተለው ጎርፍ ችግሩን እያባባሰ መሆኑ ተገልጿል።

ብሩንዲና በተለይ በታላላቅ ሃይቆች አካባቢ ያሉት ከተሞችና መንደሮች እየተጥለቀለቁ መሆናቸው ተዘግቧል።

የአየር ንብረት መለወጥና የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታዎች መዳከም ድርቁን ያስከተላቸውን መዘዞች ማባባሱን በአካባቢው የምግብ ዋስትና ላይም የተራዘመ አደጋ መደቀኑን በዓለም የምግብ ፕሮግራም የስደተኞችና የዕርዳታ ሥራዎች አስተባባሪ ፊሊክስ ኦኬች አመልክተዋል።

በምሥራቅ አፍሪካና በሌሎችም የዓለም በአካባቢዎች ያሉ ግጭቶች የምግብና የነዳጅ ዋጋ አሻቅብ ማድረጋቸውን ኦኬች ጠቁመው ሁኔታው ለማምረት የሚያስፈልገውን ወጪም ወደ መናር ሊገፋው እንደሚችል አሳስበዋል።

በአፍሪካ ቀንድ ከ15 ሚሊዮን በላይ ሰው በድርቁ መጠቃቱ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ተዘግቧል።

XS
SM
MD
LG