ዩናይትድ ስቴትስ ከዩክሬን የእህል አቅርቦት እንዲጓጓዝ ያስቻለው ውል እንዲታደስ ድርድር ሲካሄድ በሩሲያ ላይ በጣለቻቸው ማዕቀቦች የተነሳ ከሩሲያ ወደታዳጊ ሀገሮች የሚላክ የምግብ እና የማዳበሪያ አቅርቦት እንዳይደናቀፍ በመሥራት ላይ መሆኗን አስታወቀች።
በተመድ እና በቱርክ የተሸመገለው ሥምምነት በቀጣዩ ሳምንት ቅዳሜ እአአ ህዳር 19 ቀን ያበቃል።
በዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢኮኖሚ ጉዳዮች ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት ራሚን ቶሉዊ በዚህ ሳምንት ለቪኦኤ በሰጡት ቃል ሩስያ ውሉን የማታድስ ከሆነ ከባድ የሆነ የዓለም አቀፍ የምግብ ዋስትና ችግር ይደቀናል ብለዋል።
አያይዘውም "ሩሲያ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውሉን አላከብርም ባለች ጊዜ የምግብ ዋጋ በእጅጉ ማሻቀቡን እና ማክበር ስትጀምር ደግሞ በእጅጉ መቀነሱን አይተናል" ብለዋል።
የጥቁር ባህር የዕህል አቅርቦት መርኃ ግብር የተባለው እና ባለፈው ሃምሌ የተፈረመው ሥምምነት ምግብ እና ማዳበሪያ የጫኑ መርከቦች የሚያልፉበት መስመር የፈጠረ ሲሆን ሩሲያ ውሉን ማደሱ ላይ ስታመነታ ቆይታለች።
ሮይተርስ እንደዘገበው ሩሲያ ምዕራባውያን የግብርና ባንኳን የጎዳውን ማዕቀብ ቀለል እንዲያደርጉላት ጠይቃለች።
ዩናይትድ ስቴትስ ይህን የሩሲያ ጥያቄ ትቀበል እንደሆን የተጠየቁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ባለሥልጣን "ሩሲያ ለታዳጊ ሀገሮች የሚያስፈልጋቸው ምግብ እና ማዳበሪያ መላክ የሚያስችላትን ሁኔታ ለማመቻቸት የተለያዩ ሥራዎች በመሥራት ላይ ነን" ሲሉ መልስ ሰጥተዋል።