በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በትግራይ ክልል ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ በመመለስ ላይ ናቸው


በትግራይ ክልል ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ በመመለስ ላይ ናቸው
please wait

No media source currently available

0:00 0:06:00 0:00

በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት፣ በትግራይ ክልል፣ ከሦስት ዓመት በላይ ከትምህርታቸው ተስተጓጉለው የቆዩ ተማሪዎች፣ ከትላንት ጀምሮ ወደ ትምህርት ገበታቸው በመመለስ ላይ ናቸው፡፡

ይኹንና፣ አሁንም በጦርነቱ የተፈናቀሉ ዜጎች መጠለያ ኾነው በማገልገል ላይ በሚገኙና ከፍተኛ ውድመት በደረሰባቸው ትምህርት ቤቶች፣ ትምህርት ገና አለመጀመሩ ታውቋል፡፡

የክልሉ ትምህርት ቢሮ፥ ትምህርት ለመጀመር ባልተቻለባቸው ትምህርት ቤቶች፣ ኹኔታዎችን በአፋጣኝ በማመቻቸት፣ የመማር ማስተማር ሒደቱን በቅርቡ ለማስጀመር ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡ በመቐለ ከተማ ሃፀይ ዮሐንስ መሰናዶ ትምህርት ቤት ተማሪ የኾነችው ኅሊና መብራህቱ፣ ከሦስት ዓመት በላይ የተቋረጠባትንና ዳግም የጀመረችውን የ12ኛ ክፍል ትምህርቷን በመማር ላይ ሳለች ነው ያገኘኋት፡፡ ኅሊና፥ በመጀመሪያ በኮቪድ-19 ቀጥሎም በጦርነቱ ትምህርቷ ባይታጎል ኖሮ፣ በአሁኑ ጊዜ የሦስተኛ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ትኾን እንደነበር ትገልጻለች፡፡

በዛሬው ዕለት፣ እርሷ ወደ ትምህርት ገበታዋ ለመመለስ ስትበቃ፣ ጦርነቱ በፈጠረው ኹነት ምክንያት፣ የእርሷን ዕድል ለማግኘት ዕድሉ ያልደረሳቸውንና በተሟላ ኹኔታ ያላገኘቻቸውን የክፍል ጓደኞቿን አስባቸዋለች፡፡

ጦርነቱን ተከትሎ በመምህራንና በተማሪዎች ላይ የደረሰውን የሥነ ልቡና ጫና ለማቃለል እና የትምህርት ቁሳቁስ ያልተሟላላቸውን ተማሪዎች ለማገዝ ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ኅሊና ታሳስባለች፡፡ ዛሬ የተጀመረው የመማር ማስተማር ሒደትም፣ ተማሪዎች ያለትምህርት የተላለፋቸውን ጊዜ ለማካካስ በሚያስችል ሥርዓት መመራት እንደሚኖርበት አስተያየቷን አካፍላለች፡፡

የሃፀይ ዮሐንስ መሰናዶ ትምህርት ቤት ምክትል ርእሰ መምህር፣ መምህር ሰሎሞን ብርሃነ፣ በትምህርት ቤቱ፣ ትምህርት ከመቋረጡ በፊት፣ ከ1ሺሕ800 በላይ ተማሪዎች እንደነበሩት አስታውሰው፣ እስከ አሁን ከ1ሺሕ200 በላይ ተማሪዎች መመዝገባቸው ተናግረዋል፡፡በትምህርት ቤቱ፣ ለመማር ማስተማሩ ሒደት የሚረዱ ግብአቶች መውደማቸውንና ትምህርቱ ዛሬ ሊጀመር የቻለው፣ በግል ተቋማት በመታገዝ እንደኾነ የጠቀሱት ምክትል ርእሰ መምህሩ፣ በተቻለ ዐቅም ሂደቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል፡፡

የመቐለ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ በመቐለ ከተማ ትምህርት ከጀመሩ ትምህርት ቤቶች ሌላው ነው፡፡ በትምህርት ቤቱ ያገኘኋት ሜሮን ተወልደ፣ የ15 ዓመት አዳጊ ናት፡፡ በአሁኑ ጊዜ ዘጠነኛ ክፍል መድረስ ይገባት እንደነበረና በጦርነቱ ሳቢያ፣ የሰባተኛ ክፍል ትምህርቷን ለመጀመር መዘጋጀቷን ተናግራለች፡፡

በመቐለ ከተማ ቅሳነት እና ሃፀይ ዮሃንስ አንደኛ ደረጃ እንዲሁም ማይ ወይኒ ሁለተኛ ደረጃ የተባሉ ትምህርት ቤቶች፣ አሁንም፣ የተፈናቃይ ማዕከል ኾነው ነው ያገኘኋቸው፡፡ በቅሳነት ትምህርት ቤት ተጠልለው የሚገኙት አቶ እምባይነህ ዐዲሱ፤ “ሕፃናት ትምህርት እንዳይማሩ የሚያስተምራቸው የለም፡፡ ከዚህ ተነሥተን መመለስ የምንፈልገው ወደ ቀዬአችን ነው፡፡ እዚያው ተመልሰን የሚሠራው ይሠራል፤ የሚማረውም ይማራል፡፡ አሁን ግን በችግር ውስጥ ነን፡፡ በዚኽ ትምህርት ቤት ይማሩ ለነበሩ ተማሪዎች፣ የሚማሩበትን ቦታቸውን ይዘነዋል፡፡” ብለዋል።

የትግራይ ክልል የትምህርት ቢሮ ሓላፊ ዶክተር ኪሮስ ጉዕሽ፣ የትምህርት ሒደቱን ዳግም ለማስጀመር ከተጓዙበት ከቆላ ተምቤን ኹነው ለአሜሪካ ድምፅ በስልክ በሰጡት ማብራርያ፣ በክልሉ፣ ከትላንት ጀምሮ ትምህርት ቤቶች መከፈታቸውን አስታውቀዋል፡፡ ትምህርት ቤቶች በጦርነቱ የደረሰባቸው ውድመት ከፍተኛ ቢኾንም፣ ለቀጣይ ትውልድ በማሰብ፣ ድንኳን ወጥረንም ቢኾን ትምህርት እያስጀመርን ነን፤ ብለዋል፡፡

“ትምህርት ቤቶች፣ በጦርነቱ የደረሰባቸው ጉዳት በተለያየ ደረጃ የሚታይ በመኾኑ፣ በሁሉም ዘንድ ትምህርት በተመሳሳይ ቀን ዳግም ይጀመራል ተብሎ አይጠበቅም፡፡” ያሉት ዶክተር ኪሮስ “ትላንት እና ዛሬ ያልጀመሩቱ፣ በቀጣይ እንዲጀምሩ ጥረት እያደረግን ነው፡፡ በአጠቃላይ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በተረከባቸው የትግራይ ክልል አካባቢዎች፣ በሁሉም የትምህርት ደረጃዎች ትምህርቱን ዳግም ለመጀመር እየሠራን ነው፡፡” ብለዋል።

የተፈናቃዮች መጠለያ ኾነው በማገልገል ላይ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን፣ ተፈናቃዮቹን በአፋጣኝ ወደ ሌላ ቦታ በማዛወር፣ ትምህርት እንዲጀመሩ እንደሚደረግ፣ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሓላፊ ገልጸዋል፡፡ ዶክተር ኪሮስ አያይዘውም፣ ተማሪዎች ሳይማሩ የተላለፏቸውን ዓመታት ለማካካስ ታቅዶ እየተሠራ መኾኑንም አመልክተዋል፡፡

አንዱን ዓመት በአራት መንፈቀ ዘመን በመክፈል፣ የአንድ መንፈቀ ዘመንን ርዝመት ሁለት ወር ተኩል በማድረግ፣ የትግራይ ክልል ሕፃናት በዕድሜያቸው ሊደርሱበት ወደሚገባቸው የትምህርት ደረጃ እስኪደርሱ፣ በአንድ ዓመት የሁለት ዓመት ትምህርት ለማስተማር ዐቅደው እየሠሩ መኾኑን ተናግረዋል፡፡

በትግራይ ክልል፣ ትምህርት ስለ ጀመሩ ተማሪዎች እና ትምህርት ቤቶች ቁጥር የተጠየቁት የቢሮ ሓላፊው፣ እስከ አሁን ድረስ የቅበላ ምዝገባው እየተከናወነ መኾኑን ጠቅሰው፣ በቀጣይ የተሟላ መረጃ ይፋ እንደሚያደርጉ አመልክተዋል፡፡

XS
SM
MD
LG