በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከቀድሞ ካቢኔ ሥልጣን ተረከበ


የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከቀድሞ ካቢኔ ሥልጣን ተረከበ
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:37 0:00

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከቀድሞ ካቢኔ ሥልጣን ተረከበ

በቅርቡ የተዋቀረውና በፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ፣ ዛሬ ረቡዕ፣ መጋቢት 27 ቀን 2015 ዓ.ም.፣ በዶር. ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል ሲመራ ከቆየው የቀድሞው የክልሉ ካቢኔ ይፋዊ ርክክብ አካሒዷል፡፡
በርክክብ ሥነ ሥርዐቱ ላይ፣ የህወሓት ሊቀ መንበር ዶር. ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል፣ “ከዐዲሱ ካቢኔ ጋራ ተባብረን እንሠራለን፤” ብለዋል፡፡
የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ፣ ከርክክቡ በኋላ በሰጡት መግለጫ፣ ከፌዴራሉ መንግሥት ጋራ የተሻለ መተማመን ላይ መደረሱን አስታውቀዋል፡፡
አያይዘውም፣ ከኤርትራ መሪዎች ጋራ፣ በሰላማዊ መንገድ ችግሮችን ለመፍታት፣ “በመልካም ጉርብትና ለመሥራት ዝግጁ ነን፤” ሲሉ ተናግረዋል፡፡በትግራይ ክልል የተቋቋመው ዐዲሱ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ ከቀድሞው አስተዳደር በይፋ ርክክብ በመፈጸም፣ በዛሬው ዕለት ሥራውን ጀምሯል፡፡ በመቐለ ከተማ በተካሔደው የርክክብ ሥነ ሥርዐት ላይ፣ ላለፉት አምስት ዓመታት፣ የትግራይን ክልል ሲመሩ የቆዩት ዶር. ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል፣ ከዐዲሱ ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ ጋራ ተባብረው እንደሚሠሩ ድጋፋቸውን ገልጸዋል፡፡

ከመንግሥት ምንም ሳትጠብቁ፣ ኹሉንም ችግር ተቋቁማችኹ፣ ባላችኹ ዐቅም የመመከት ሒደቱ ውጤታማ እንዲኾን የሚቻላችኹን ኹሉ አድርጋችኋል፤ ብዙ መሥዋዕትም ከፍላችኋል፤ እንደ አመራርም ብዙ ችግር ተሸክማችኹ መጥታችኋል፡፡ ለሕዝባችኹ እና ለመንግሥታችኹ ክብር በመታገላችኹ ልትኮሩ ይገባል፡፡"

"ከመንግሥት ምንም ሳትጠብቁ፣ ኹሉንም ችግር ተቋቁማችኹ፣ ባላችኹ ዐቅም የመመከት ሒደቱ ውጤታማ እንዲኾን የሚቻላችኹን ኹሉ አድርጋችኋል፤ ብዙ መሥዋዕትም ከፍላችኋል፤ እንደ አመራርም ብዙ ችግር ተሸክማችኹ መጥታችኋል፡፡ ለሕዝባችኹ እና ለመንግሥታችኹ ክብር በመታገላችኹ ልትኮሩ ይገባል፡፡" ብለዋል።

የጊዜያዊ አስተዳደሩ ጽሕፈት ቤት ሓላፊ አቶ ዐማኑኤል አሰፋ፣ ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ማብራርያ፣ አስተዳደሩ፣ ከስድስት ወራት እስከ አንድ ዓመት ይቆያል፤ ብለዋል፡፡ የተዋቀረው የጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ፣ 27 አባላት እንዳሉትና ከ51 በመቶ በላይ ከህወሓት፣ 49 በመቶ ደግሞ ከትግራይ ኃይሎች፣ ከምሁራንና ከባይቶና ፓርቲ የተውጣጡ እንደኾኑ ገልጸዋል፡፡

በተደረገው የካቢኔ አባላት የሓላፊነት ምደባ፣ ሌፍተናንት ጀነራል ታደሰ ወረደ፥ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የሰላም እና የጸጥታ ዘርፍ ሓላፊ፤ ሌፍተናንት ጀነራል ጻድቃን ገብረ ትንሣኤ፥ ምክትል ፕሬዝዳንት እና ያልተማከለ አሰተዳደር እና ዴሞክራታይዜሽን ዘርፍ ሓላፊ ኾነው ተሾመዋል፡፡

የባይቶናን ፓርቲ በመወከል የካቢኔው አባል የኾኑት አቶ ታደለ መንግሥቱ፣ የክልሉ የትራንስፖርት እና የመገናኛ ቢሮ ሓላፊ ኾነው ተሾመዋል፡፡ “በትግራይ፣ እንኳን የተቃዋሚ ፓርቲ አባል ኾኖ ወደ መንግሥት ካቢኔ ሊገባ፣ ተቃዋሚ ፓርቲ ኾኖ ለመሥራትም አስቸጋሪ ኾኖ ቆይቷል፤” በማለት ምደባውን የተቀበሉት አቶ ታደለ፣ አሁን የተገኘው አጋጣሚ፣ ከሕዝብ ጋራ ለመቀራረብ እንደሚያግዛቸው ገልጸዋል፡፡

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ፣ ከርክክቡ በኋላ በሰጡት መግለጫ፣ አስተዳደሩ፣ ቅድሚያ በመስጠት በአፋጣኝ የሚያከናውናቸውን ተግባራት ጠቁመዋል፡፡ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ተዋጊዎች፣ በቂ ሕክምና የሚያገኙበትና መልሰው የሚቋቋሙበት ሥራ እንደሚጀመር የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ፣ ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው የሚመለሱበትና በሕገ መንግሥቱ በሚታወቅ ኹሉም የትግራይ መሬት፣ አስተዳደራዊ መዋቅርን የመዘርጋት ሥራ እንደሚሠራ አስታውቀዋል፡፡

ከፌዴራሉ መንግሥቱ ጋራ ክልሉ ያለውን ግንኙነት በተመለከተ፣ የመተማመን ሒደቱ በየጊዜው እየጨመረ እንደኾነ፣ አቶ ጌታቸው በመግለጫቸው አመልክተዋል፡፡

መጠራጠሩን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት ጊዜ እንደሚጠይቅ የታወቀ ነው፡፡ የነበረው ያለመተማመን፣ በአሁኑ ጊዜ በተሻለ መልኩ እየተቀረፈ፣ በአንዳንድ ጉዳዮች የጋራ መግባባት መፍጠር እንደምንችል መገንዘብ ጀምረናል፡፡"


"መጠራጠሩን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት ጊዜ እንደሚጠይቅ የታወቀ ነው፡፡ የነበረው ያለመተማመን፣ በአሁኑ ጊዜ በተሻለ መልኩ እየተቀረፈ፣ በአንዳንድ ጉዳዮች የጋራ መግባባት መፍጠር እንደምንችል መገንዘብ ጀምረናል፡፡" ያሉት አቶ ጌታቸው "በዚኽም፣ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል፣ ያለመተማመኑም ቢኖር፣ የጀመርናቸው መልካም ግንኙነቶች አሉ፡፡" ብለዋል።

በፌዴራሉ መንግሥት፣ ሥራ ለማስጀመር የሚያስችል በጀት ለክልሉ መለቀቁን የገለጹት አቶ ጌታቸው፣ ምን ያህል ገንዘብ እንደተፈቀደ ግን ይፋ አላደረጉም፡፡ ከሰኔ ወር 2013 ዓ.ም. ጀምሮ፣ ወደ ክልሉ በጀት ሳይላክ መቆየቱንና ይኸው በጀት ተሟልቶ እንዲደርሰን መጠየቃችንን እንቀጥላለን፤ ብለዋል፡፡

የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት፣ ከጥቂት ቀናት በፊት፣ በክልሉ ቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው፣ ከትግራይ ክልል ጋራ በሕጋዊ እና በሰላማዊ መንገድ ግንኙነትን የማሻሻል ፍላጎት እንዳለ የገለጹትን በማስመልከት፣ አቶ ጌታቸው ተጠይቀው፣ ስለ ሰላም ማውራታቸው፣ የሰላማዊ ሓሳብ ለውጥ መምጣቱ መልካም እና የሚበረታታ እንደኾነ ጠቅሰዋል፡፡

አያይዘውም፣ በትግራይ ክልል በኩል፣ “ጥያቄ ካለ በሕጋዊ መንገድ መልስ መስጠት ይቻላል፤” እንዳልነው ኹሉ፣ በአማራ ክልልም በኩል፣ ጥያቄ ካለ በሕጋዊ መንገድ መመለስ አለበት፤ ሊባል እንደሚገባው አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ በሕገ ወጥ መንገድ የተወሰደ መሬት እና ንብረት መመለስ ይገባዋል፤ በማለት አስተያየታቸውን በአጽንዖት አስቀምጠዋል፡፡ ጊዜያዊ አስተዳደራቸው፣ ከሌላ ከማንኛውም አካል ጋራ የሚያደርገውን ግንኙነት፣ የሕዝባችንን ስሜት እና ጉዳት በማያሳንስ መልኩ እንደርገዋለን፤ ሲሉም አክለዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት፣ “ሸኔ” እያለ የሚጠራቸው እና ራሳቸውን “የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት” ብለው ከሚጠሩ ኃይሎች ጋራ የነበራችኹ ግንኙነት፣ በአሁኑ ጊዜ ምን ይመስላል? በሚል ከቪኦኤ ለቀረበላቸው ጥያቄም ሲመልሱ፤
"የፌደራሉ መንግሥት፣ ከኦሮሞ ታጣቂዎች ጋራ የጀመረውን የሰላም ውይይት፣ በሙሉ ልባችን እንደግፋለን፡፡ ወደ ሰላማዊ መንገድ ፈጥነው እንዲገቡና መላው የኦሮሞ ሕዝብ በመረጋጋት ኑሮውን እንዲቀጥል ነው የምንሻው፤ ለራሳችን የምንፈልገውን ነው ለኦሮሞ ሕዝብም የምንመኘው፡፡" ከማለት ውጪ ከታጣቂው ቡድን ጋር ተያይዞ ለተነሳው ጥያቄ ቀጥተኛ ምላሽ ሳይሰጡ አልፈዋል።

የፌደራሉ መንግሥት፣ ከኦሮሞ ታጣቂዎች ጋራ የጀመረውን የሰላም ውይይት፣ በሙሉ ልባችን እንደግፋለን፡፡ ወደ ሰላማዊ መንገድ ፈጥነው እንዲገቡና መላው የኦሮሞ ሕዝብ በመረጋጋት ኑሮውን እንዲቀጥል ነው የምንሻው፤ ለራሳችን የምንፈልገውን ነው ለኦሮሞ ሕዝብም የምንመኘው፡፡"


ባለፈው ሳምንት፣ ከፌዴራሉ መንግሥት እና ከኦሮሚያ ክልል አመራሮች ጋራ፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራሮች ውይይት ማካሔዳቸውን ያወሱት አቶ ጌታቸው፣ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት፣ በግብርና፣ በጤና እንዲሁም በትምህርት ዘርፎች ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባቱንና ከትላንት ጀምሮ ደግሞ፣ ከክልሉ ወደ ትግራይ ክልል ማዳበርያ እና ምርጥ ዘር መጓጓዝ መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡

የኤርትራ መንግሥትን አመራሮች አስመልክቶም በሰጡት አስተያየት፤ "ከማንኛውም ኃይል ጋራ ሰላም እንፈጥራለን፤ ቁስላችንን ማከክ አንፈልግም፤ ያልነው ኤርትራንም የሚመለከት ነው፡፡ በእኛ እምነት፣ ርግጠኛ ባልኾንም፣ ከኤርትራ አመራሮች፣ ጤነኞች አይታጡም፤ ይህ ጉዳይ እንደማያዋጣ አውቀው፣ እስከ አሁን የተፈጸመ በደል ይበቃል፤ ብለው፣ ወደ ሰላማዊ ወንድማማችነት እና ጉርብትና የሚመለሱበት ኹኔታ ካለ፣ ቢያጤኑት የሚል ሓሳብ አለኝ፡፡" ብለዋል።
ከትግራይ ክልልም ኾነ ከዓለም አቀፍ ተቋማት በጦርነቱ ውቅት በኤርትራ መንግሥት ወታደሮች ተፈፅመዋል ስለተባሉት የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ማስተባበያ የሚሰጠው የኤርትራ መንግሥት በዛሬ በአቶ ጌታቸው መግለጫ ላይ ያለው ነገር የለም።
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በቅርቡ ባወጣው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን በሚገመግመው ዓመታዊ ሪፖርቱ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ውስጥ የተሳተፉ ኹሉም ኃይሎች የጦር ወንጀል መፈፀማቸው ተረጋግጧል ሲል ሪፖርት አውጥቷል። አቶ ጌታቸው ተጠያቂነትን በተመለከተ ማብራሪያ ሲሰጡ በአገር ውስጥ አካታች የኾነ የፍትሕ ሥርዐት ቢዘረጋ እንኳን፣ ጦርነቱ፣ የውጭ ኃይል የተሳተፈበት ስለኾነ፣ ዓለም አቀፋዊ የኾነ ሒደትን የሚጠይቅ ነው፤ ብለዋል፡፡

XS
SM
MD
LG