ዋሺንግተን ዲሲ —
ታሊባን ባለፈው ወር ወንዶች ብቻ የተያዘውን ካቢኔውን ይፋ ባደረገበት ጊዜ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በከባዱ የነቀፈ ቢሆንም ዛሬም ሴቶች የሌሉበት ምክትል ሚኒስትሮች ሾመት ሰጥቷል።
የተሿሚዎቹን ዝርዝር ዛሬ የመንግሥቱ ቃል አቀባይ ዛቢሁላ ሙጃሂድ ካቡል ላይ በተጠራ ጋዜጣዊ ጉባዔ ይፋ አደርገዋል። ታሊባን በድጋሚ ወንዶች ብቻ መሰየሙ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጩኽት ደንታ እንደሌለው የሚያሳይ እንደሆነ ተገልጧል። ቀደም ሲል አስተዳደራችን አሳታፊ ይሆናል፤ የሴቶች መብት እናከብራለን ብሎ ቃል ቢገባም በያዘው አክራሪ አቋም መቀጠሉን የሚጠቁም እንደሆኑ አመላካች ነው ተብሏል።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ታሊባንን የሚመዝነው በሚወስዳቸው እርምጃዎች እንደሚሆን እና ታሊባን መር መንግሥት ዕውቅና ማግኘት አለማግኘቱን የሴቶችና ህዳጣን ክፍሎች አያያዙ ይወስነዋል ብሎ ማስጠንቀቁ ይታወሳል።