አልሸባብ የተባለው የሽብርተኞች ቡድን በሶማልያ ምክር ቤት ላይ ዛሬ ለደረሰውና ቢያንስ ስድስት ሰዎች ለቆሰሉበት የሞርተር ጥቃት ኃላፊነቱን እንደሚወስድ አስታወቀ፡፡
የሞርተር ጥቃቱ የተካሄደው በሶማልያ አዲስ የተመረጡት የምክር ቤት አባላት የምክር ቤቶቹን አፈ ጉባኤዎች ለመምረጥ ዛሬ ሰኞ ስብሰባ በተቀመጡበት ወቅት ነው፡፡
ህግ አውጭውና ፕሬዚዳንታዊው ዕጩ አብዱረህማን ዋርሳሜ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት "በተካሄዱ ተከታታይ ዙር የሞርተር ጥቃቶች የሳቸውን ሁለት ጠባቂዎች ጨምሮ በርካታ ሰዎች መቁሰላቸውን" ገልጸዋል፡፡
አማጺው የሶማሊያ የአልሸባብ ቡድን ባወጣው የመገናኛ ብዙሃን ዘገባ ኃላፊነቱን እንወሚወስድ አስታውቋል፡፡ የሶማልያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሞሀመድ ሀሰን ሮብሌ “የሽብርተኞች ድርጊት” ያሉትን ጥቃት አውግዘዋል፡፡
በማህበራዊ ድረ ገጻቸው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት በተዘዋዋሪ ውክልና የተካሄደውን "የሶማልያ ምርጫ በማጠናቀቅ ላይ የሚገኙትን የፓርላማ አባላትን ለማስፈራራት በፈሪዎች የተካሄድ የሙከራ ጥቃት ነው" ብለውታል፡፡
ሮብሌ የምርጫውን ሂደት ለማፋጠን ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኙትን የምክር ቤት አባላት አድንቀዋል፡፡ ዛሬ ሰኞ ጥቃቱ ከመካሄዱ በፊት ህግ አውጭዎቹ የላይኛውን ምክር ቤት አፈጉባኤ እኤአ በሚያዝያ 26 የታችኛውን ምክር ቤት አፈጉባኤ ደግሞ ከዚያ በኋላ ለመምረጥ በሙሉ ድምጽ ተስማምተዋል፡፡
በቀጥተኛ ውክልና ሳይሆን በተዘዋዋሪ የተካሄደው የሶማልያ ምርጫ በጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ፎርማጆ ተብለው በሚታወቁት በፕሬዚዳንት ሞሀመድ አብዱላሂ ሞሃመድ መካከል ለወራት ሲካሄድ በቆየው ሽኩቻ ሳይካሄድ መቆየቱ ይታወሳል፡፡
ፎርማጆ የሥልጣን ዘመናቸውን ለማራዘም ፍላጎቱ የነበራቸው ቢሆንም በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ግፊት ወደ ኋላ እንዲያፈገፍጉ አድርጓቸዋል፡፡
አልሸባብ የፖለቲካውን አለመረጋጋት እንደ አጋጣሚ በመውሰድ ተከታታይ ጥቃቶችን በሶማልያ የደህንነት እና የፖለቲካ ሰዎች ላይ ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡
የሶማልያ ህግ አውጭዎች እስከ ሚቀጥለው ግንቦት ድረስ ለሚቀጥለው ፕሬዚዳንት ድምጽ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡