የናይጄሪያው ፕሬዝደንት ሙሃማዱ ቡሃሪ ሥልጣናቸው ከመጠናቀቁ አንድ ሳምንት ሲቀረው፣ በአፍሪካ ትልቁ ነው የተባለለትን የነዳጅ ማጣሪያ ዛሬ መርቀው ከፍተዋል። ማጣሪያው ከዓመታት መዘግየት በኋላ መጠናቀቁ ተገልጿል።
በአፍሪካ አንድ ቁጥር ባለሃብት በሆኑት አሊኮ ዳንጎቴ በንግድ መዲናዋ ሌጎስ የተገነባው የነዳጅ ማጣሪያ በሙሉ አቅሙ ሲንቀሳቀስ፣ በቀን 650 ሺሕ በርሜል ያጣራል ተብሏል። በመጪው ሰኔ ሥራውን እንደሚጀምርም ታውቋል።
በመንግስት የሚተዳደሩት የነዳጅ ማጣሪያዎች በበቂ ባለማምረታቸው ምክኛት፣ በአፍሪካ በሕዝብ ቁጥር ቀዳሚ የሆነችውና ድፍድፍ ነዳጅም በብዛት የምታመርተው ናይጄሪያ፣ ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚያስፈልጋትን ነዳጅ ከውጪ ስታስገባ ቆይታለች፡፡
19 ቢሊዮን ዶላር የፈጀው ማጣሪያ ለነዳጅ የሚወጣውን የውጪ ምንዛሪ እንደሚያስቀርና፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ይጠበቃል።
ከነዳጅ ማጣሪያው ጋር ተያይዞ በ 2 ቢሊዮን ዶላር የተገነባው የማዳበሪያ ፋብሪካም፣ በዓመት ሶስት ሚሊዮን ቶን ማዳበሪያ የማምረት አቅም እንዳለው የኤኤፍፒ ዘገባ አመልክቷል።