የእስራኤል እና የፍልስጤም የህዝብ ተወካዮች በመካከለኛው ምስራቅ የሰላም ጥረቶች ለአስርታት አጣብቂኝ ውስጥ ከቆየው አለመግባባት ያስወጣ እና ወደፊት ያራምድ ዘንድ ተስፋ ያሳደሩበትን የሁለት መንግሥታት ኮንፌዴሬሽን ሃሳብ አዲስ ረቂቅ አቀረቡ።
በርካታ አወዛጋቢ ሃሳቦችን ያካተተው እቅድ በሁለቱም በኩል ካሉ መሪዎች ዘንድ ድጋፍ ያገኝ እንደሆን እስካሁን ግልፅ አይደለም። ይሁንና ግጭቱን አስመልክቶ የሚካሄዱ ክርክሮችን ለመቅረጽ ሊረዳ ይችል ይሆናል። በያዝነው ሳምንት ለአንድ የዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ባለሥልጣን እና ለተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሃፊ እንደሚቀርብ ተጠብቋል።
እቅዱ በአብዛኛው እስራኤል እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ1967 የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ወቅት በኃይል በያዘቻቸው የዌስት ባንክ፣ ጋዛ እና ምስራቃዊ እየሩሳሌም ግዛቶች የፍልስጤም ነፃ ግዛት እንዲመሰረት ይጠይቃል።
እስራኤል እና ፍልስጤም ሁለት የተለያዩ ነገር ግን ፀጥታን እና መሠረተ ልማትን በሚመለከቱ እና ሌሎች በሁለቱም ህዝቦች ፍላጎቶች ላይ ተጽዕኖ በሚያሳድሩ ጉዳዮች ዙሪያ በከፍተኛ ደረጃ መተባበር የሚፈቅድ መንግሥታት ሊኖራቸው ይችላል።
እቅዱ በተጨማሪም በእስራኤል በተያዘው የዌስት ባንክ ቁጥራቸው አምስት መቶ ሺህ የሚደርሱ የአይሁድ ሰፋሪዎችም ባሉበት መቆየት እንዲችሉ ይፈቅዳል። በድንበር አቅራቢያ ያሉ ግዙፍ ሰፈሮችም በተናጠል በሚደረጉ የመሬት ልውውጦች በእስራኤል ሥር እንዲካለሉ ይጠይቃል።
በሌላ በኩል በዕቅዱ መሰረት በማዕከላዊ ዌስት ባንክ የሚኖሩ ሰፋሪዎች ቋሚ የፍልስጤም ነዋሪ የመሆን አለያም ወደሌላ አካባቢ የመዛወር አማራጭ ይሰጣቸዋል። እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ1948 እስራኤል በተዋቀረችበት ወቅት በተካሄደው ጦርነት የተፈናቀሉ ተመሳሳይ ቁጥር ያላቸው ፍልስጤማውያንም በእስራኤል ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸው የፍልስጤም ዜጎች የመሆን አለያም ወደ ሌላ አካባቢ የመዛወር ዕድል እንዲኖራቸው ይፈቅድላቸዋል።
አዲሱ ውጥን በአመዛኙ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2003 ዓም የቀድሞ ባለሥልጣናትን ጨምሮ በታዋቂ እስራኤላውያን እና ፍልስጤማውያን የተረቀቀው መጠነ ሰፊውን እና ሁሉን አቀፉ የጄኔቫ ሥምምነት ላይ የተመሰረተ የሰላም እቅድ ነው። 100 የሚደርሱ ገጾች ያለው የኮንፌዴሬሽን እቅድ ልዩ ትኩረት ለሚሹ ዋናዋና ጉዳዮች ለመቅረፍ የሚያስችሉ ዝርዝር ምክረ-ሃሶቦችን ያካትታል።
የጄኔቫ ዕቅድ በመባል የሚታወቀውን ውጥን በተባባሪነት ያቋቋሙት የቀድሞው የእስራኤል ከፍተኛ ባለሥልጣን እና የሰላም ተደራዳሪ ዮሲ ቤይሊን ሰፋሪዎችን በጅምላ የማውጣቱን ሃሳብ መተው ዕቅዱን ተቀባይነት ያሰጠዋል ብለዋል።
የእስራኤል የፖለቲካ ሥርዓት በሰፋሪዎች እና በደጋፊዎቻቸው የበላይነት የተያዘ ሲሆን፤ ዌስት ባንክን የመጽሐፍ ቅዱስ መሰረት እንዳለው እና ታሪካዊ የአይሁድ ሕዝብ ማዕከላዊ ግዛት፣ የእስራኤል ዋና አካል አድርገው ይመለከታሉ።