በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ፌስቡክ የጥላቻ ንግግሮችን የያዙ ማስታወቂያዎችን ይለይ እንደሆነ በቀረበለት ፈተና እንደገና ወደቀ


ፎቶ ፋይል - የፌስቡክ ሜታ አርማ፤ ካሊፎርኒያ የሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት።
ፎቶ ፋይል - የፌስቡክ ሜታ አርማ፤ ካሊፎርኒያ የሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት።

ዓለም አቀፉ የማኅበራዊ ትስስር ድረ ገጽ ፌስቡክ፤ የጥላቻ ንግግሮችን የያዙ ማስታወቂያዎችን ይለይ እንደሆነ ግሎባል ዊትነስ (Global Witness) በተሰኘ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት የቀረበለትን ፈተና ወድቋል።

ድርጅቱ ለፈተና የላካቸው ማስታወቂያዎች በአማራ፣ በኦሮሞና በትግራይ ተወላጆች ላይ ግድያ እንዲፈጸም የሚቀሰቅሱ ጥሪዎችን የያዙ ማስታወቂያዎች ሲሆኑ ፌስቡክ ግን ለይቶ ሊያስቀራቸው አልቻለም።

ፌስቡክ በተመሳሳይ ከዚህ በፊት በማይናማር ውስጥ ግድያ እንዲፈጸም የሚወተውቱ ማስወቂያዎች በግሎባል ዊትነስ ተልኮለት ሳይዛቸው ቀርቷል። አሁን ኢትዮጵያን በሚመለከት የተላከለት ሲጨመርበት ድርጅቱ ለሁለተኛ ግዜ ፈተናውን ወድቋል። ነገሩን የከፋ የሚያደርገው በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የቀረበለትን ፈተና የወደቀው በመጀመሪያ በማይናማር ሙከራ ወቅት የተገኙትን ውጤቶች ግሎባል ዊትነስ በሪፖርት ለፌስቡክ ካሳወቀው በኋላ መሆኑ ነው።

በመሆኑም ፌስቡክ እና እናት ድርጅቱ ሜታ፤ አደገኛ የጥላቻ ንግግሮችን የመለየት ችሎታቸውን ለማወቅ የቀረበላቸውን ፈተና መውደቃቸውን ድርጅቱ ይፋ አድርጓል።

ፈታኙ ድርጅት “መያዝ የነበርባቸው አደገኛ ቅስቀሳዎች ሳይያዙ ቀርተዋል” ብሎ ለፌስቡክ ባስታወቀበት ጊዜ ፌስቡክም መልዕክቶቹ ፍቃድ ማግኘት እንዳልነበረባቸው አምኖ ከዚህ በፊት የያዛቸውን ሌሎች የጥላቻ መልዕክቶችን አሳይቷል።

ከአንድ ሳምንት በኋላ ግን ግሎባል ዊትነስ በድጋሚ ሁለት ተጨማሪ የጥላቻ ጹሑፎችን በአማርኛ ለፌስ ቡክ ሲልክ፣ መልዕክቶቹን እንዲለጠፉ ፈቃድ አግኝተዋል።

ከድርጅቱ ለፌስቡክ ለፈተና የተላኩት የጥላቻ ንግግሮች በኢትዮጵያ ላይ ያተኮሩ፣ ፍራንስስ ሁገን የተባሉ ባለሞያ ከዚህ በፊት ባወጡት የውስጥ ሰነድ ላይ የተጠቀሰው እና፤ “የፌስቡክ የተዝረከረከ አሠራር በኢትዮጵያ የጎሳ ግጭትን አያባባሰ ነው” በሚለው ላይ ያተኮሩ ነበሩ። ፍራንስስ ሁገን ባለፈው ዓመት ጉዳዩን በተመለክተ ለአሜሪካ ምክር ቤት ምስክርነታቸውን አቅርበው ነበር።

በግሎባል ዊትነስ 12 በጽሑፍ የተዘጋጁ ክብርን የሚነኩና በኢትዮጵያ የሚገኙ ሦስት ብሔሮች ማለትም አማራ፣ ኦሮሞ እና የትግራይ ተወላጆች ላይ ግድያ እንዲፈጸም የሚወተውቱ ማስታወቂያዎችን እንዲያስተላልፍ ለፌስቡክ ተልኮለት ለመተላለፍ ፈቃድ አግኝተዋል።

ማስታወቂያዎቹ ግን ለፈተና ያህል የተላኩ በመሆናቸው በፌስቡክ ላይ አልወጡም። በማይናማር ጉዳይ ላይ የተደረገውም ተመሳሳይ ሙከራ ነበር።

ሜታ በኢሜይል በሰጠው መልስ “ኢትዮጵያን በተመለከተ ለምናደርገው የጥንቃቄ ሥራ የሃገር ውስጥ ጉዳይን የሚያውቁ ብዙ የሰው ኃይል መድበናል። ይህ ብብዛት የሚነገረውን የአማርኛ ቋንቋ ይጨምራል” ብሏል። ማሽኖችና ሰዎች ሁሌም ስህተት ሊሠሩ ይችላሉ ሲል አክሏል በኢሜይሉ።

የፌስቡክ እናት ድርጅት ሜታ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪ ባልሆኑ እንደ ኢትዮጵያና ማይናማር ለመሰሉ በግጭት ውስጥ የሚገኙ ሀገሮችን በተመለከተ የሚለጠፉ ጽሑፎችን የሚቆጣጠሩ ስንት ባለሞያዎች እንዳሉት ለመናገር ፈቃደኛ አይደለም።

ባለፈው ኅዳር ፌስቡክ ወደ መዲናዋ በመቃረብ ላይ የነበረውን የትግራይ ጦር ዜጎች “እንዲቀብሩ” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጥሪ ያደረጉበትን ጹሑፍ አንስቷል።

በዛ ከፌስቡክ ላይ በተነሳው ጽሑፋቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “ሁላችንም ለኢትዮጵያ የመሞት ግዴታ አለብን” ካሉ በኋላ ለዚህም ዜጎች “የተገኘውን መሳሪያ ይጠቀሙ” ብለው ነበር።

4.1 ሚሊዮን ተከታይ ያላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በፌስ ቡክ ላይ መጻፋቸውን ቀጥለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የትግራይ ኃይሎችን “ካንሰር” እና “አረም” ብለው ከጠሩ በኋላ አሜሪካና አጋሮቿ ክብርን የሚነኩ ንግግሮችን በተመለከተ ኢትዮጵያን አስጠንቅቀዋል።

ከግሎባል ዊትነስ ጋር በምርመራው ላይ የተሳተፈው ፎክስግላቭ ኃላፊ ሮዛ ከርሊንግ“በማይናማር የዘር ማጥፋት ከተፈጸመ ከዓመታት በኋላ፣ ፌስቡክ ትምህርት እንዳላገኘ ግልጽ ነው” ብለዋል።

XS
SM
MD
LG