በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኞች ታሰሩ


ፎቶ ፋይል፦ አዲስ አበባ /ኢትዮጵያ/
ፎቶ ፋይል፦ አዲስ አበባ /ኢትዮጵያ/

የተባበሩት መንግሥታት ዛሬ ረቡዕ ባወጣው መግለጫ፣ ጦርነት ውስጥ ባለቸው ሰሜን ኢትዮጵያ፣ ለዓለም ምግብ ፕሮግራም የሚሰሩ 72 አሸከርካሪዎች መታሰራቸውን አስታውቋል፡፡

ይህ መግለጫ የወጣው፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ በኢትዮጵያ የሚሰሩት 22 የድርጅቱ ሠራተኞች፣ በትግራይ ተወላጆች ላይ የሚደረገውን የእስር ዘመቻ ተከትሎ፣ አዲስ አበባ ውስጥ በፌዴራል መንግሥቱ ታስረዋል ሲል ትናንት ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ ካስታወቀ በኋላ ነው፡፡

የመንግሥታቱ ድርጅት ቃል አቀባይ፣ ስቴፋን ዱጃሪች “ከዓለም የምግብ ፕሮግራም ጋር በኮንትራት የሚሰሩ 72 አሸከርካሪዎች፣ በአፋር ክልል ዋና ከተማ፣ ሰመራ ውስጥ መያዛቸውን አረጋግጠናል፡፡ የታሰሩበንትም ምክንያት እንዲያስረዱን ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር እየሠራንበት ነው፡፡” ብለዋል፡፡

በመንግሥታቱ ድርጅቱ ሥር በሚገኙ፣ የተለያዩ ተቋማት የሚሠሩት ሠራተኞች፣ ስለታሰሩበት ምክንያት የተገለጸ ነገር አለመኖሩንም የገለጹት ቃል አቀባዩ፣ መንግሥት የታሰሩት ሠራተኞ ደህንነት የተጠበቀና የተሟላ የህግ ከለላ እንዲሰጣቸው እንዲያደርግ እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

አንዳንዶቹ ከታሰሩ ጥቂት ቀናት ያለፋቸው መሆኑን ቃል አቀባዩ የገለጹ ሲሆን፣ 6 ሰዎች ሲለቀቁ፣ 16ቱ ግን አሁንም በእስር ላይ መሆናቸው ተመልክቷል፡፡

በእስር የቀሩት በተባበሩት መንግሥታት የደህንነት ባለሥልጣናት የተጎበኙ መሆናቸውም ተገልጿል፡፡

በአፋር፣ ሰመራ የታሰሩት አሸከርካሪዎች የብሄር ማንነታቸው በግልጽ ተለይተው ያልታወቀ መሆኑም በዘገባው ተጠቅሷል፡፡

እኤአ መስከረም 30፣ ሰባት የተባበሩ መንግሥታት ድርጅት ሠራተኞች በአገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብተዋል ተብለው ካገር የተባረሩ መሆናቸው ይታወቃል፡፡

በትናንትናው እለት ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው አስተያታቸውን የሰጡት የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ እንዲህ ብለዋል

“ይህ የተረጋገጠ ከሆነ ፣ እኛም የብሄር ማንነትን መሠረት በማድረግ የተይዙትን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኞችን እስር እናወግዛለን፡፡ እርስዎ ከጠቀሱት ሪፖርት እንደምንረዳው እነዚያ የታሰሩ ሰዎች የትግራይ ተወላጆች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት የጸጥታ ኃይሎች የብሄር ማንነትን መሰረት አድርገው የሚያደርሱት ወከባና ጥቃት በፍጽሙ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ ከህወሃት ጋር ግ ንኙነት ባላቸው የትግራይ ኃይሎችና አማጽያንም የሚያደርሱትን የበቀል ጥቃት እኩል እናወግዛለን፡፡ ሁሉም ወገኖች ከ እንደዚያ ያለ ድርጊት ተቆጥበው የሰብአዊ መብትና የህግ የበለያነት እንዲያከበሩ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡”

የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት በበኩሉ፣ መንግሥት ወደ አካባቢው የሚላከው እርዳታ እንዳይደርስ በማድረጉ፣ በትግራይ ክልል የምግብና የነዳጅ እጥረት መከሰቱን አመልክቷል፡፡

ጦርነቱ ሙሉ ለሙሉ ወደ እርስ በርስ ጦርነት ከማምራቱ በፊት፣ በትግራይ ላለው ግጭት፣ የፖለቲካ መፍትሄ ለመስጠት የሚደርገው ጥረት እድሉና ጊዜው እየጠበበ መምጣቱንም ምክር ቤቱ አስታውቋል፡፡

ትናንት በዩናይትድ ስቴትስና ግብጽ የጋራ ምክክር ላይ፣ ከግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር ተገናኝተው በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ መነጋገራቸውን ያወሱት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ አንተኒ ብሊንከንም በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ይህን ብለዋል

“በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ በአፍሪካ ቀንድ ያለውን መረጋጋት ለአደጋ አጋልጦታል፡፡ ከአጋሮቻችን ጋር ሆነን፣ በአካባቢው ያሉ ሁሉም ወገኖች፣ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ፣ ተኩስ በማቆም፣ ለሰላማዊ ድርድር እንዲቀመጡ የምናደርገውን ማበረታት እንቀጥላለን፡፡”

መፍትሄ ለማፈላለግ የተለያዩ ወገኖችን በማነጋገር ላይ የሚገኙት ፣ በአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሊሲጉን ኦባሳንጆ፣ ትናንት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ “ለፖለቲካዊ መፍትሄ እድሉ ቢኖርም፣ ያለችው ቀዳዳ ግን በፍጥነት እየጠበበች ነው” ብለዋል፡፡

XS
SM
MD
LG