በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ጠ/ሚ ዐቢይ ወደ ጽ/ቤታቸው ተመለሱ የመጀመሪያውን ዙር ዘመቻ አሳክተናል አሉ


ፎቶ ፋይል፦ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ አህመድ
ፎቶ ፋይል፦ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ አህመድ

"በዕቅዳችን መሠረት የመጀመሪያውን ምዕራፍ፣ ዘመቻ በሁለት ሣምንት ውስጥአሳክተናል" ያሉት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ አህመድ ለተወሰኑ ጊዚያት ወደ ቢሮ መመለሳቸውን በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ አስታውቀዋል።

"በድል የታጀበው የመጀመሪያው ምዕራፍ" በሚል ርዕስ የወጣዉ መግለጫቸው የእስካሁኑ ሂደት ኢትዮጵያን ቀናያደረገ መሆኑን አመልክቷል።

ሆኖም ትግሉ ገና አለመጠናቀቁን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒሰትሩ "ነጻ ያልወጡ አካባቢዎች አሉን።" በማለትም አክለዋል ።

በጦር ሜዳ ተሸነፈ መባሉን ያልተቀበሉት የህወሓት መሪዎች ስልታዊ ማፈግፈግ ማድረጋቸውን ገልፀዋል።

የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ስለለቀቋቸው ከተሞች በትዊተር ገፃቸው ላይ በትናንትናው ዕለት በትዊተር ገፃቸው ላይ ባወጡት ጹሑፍ፤ ሰሜን ሸዋን ኮምቦልቻንና ደሴን የለቀቁት በእቅዳቸው መሰረት መሆኑን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዛሬ ጹሑፋቸው፤ "አሁን የፈተነን ኃይል ዳግመኛ የኢትዮጵያ ፈተና ሆኖ እንዳይመጣ የሚያስችል ዘላቂ መፍትሔ ልንሰጠው ይገባል።” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒሰትሩ "ኢትዮጵያ የሚለውን የነጻነት ስም የማስጠበቅ የታሪክ አደራ አለብን" በሚል የሃገሪቱን ጦር ለመምራት ወደ ግንባር የዘመቱት ከሁለት ሳምንታት በፊት ነበር።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ የተነቃቁና ጥሪያቸውን የተቀበሉ በርካታ ታዋቂ ሰዎችና ሌሎች ዜጎችም ፈለጋቸውን በመከተል ወደተለያዩ ግንባሮች አምርተዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሰሜን ሸዋ፣ ከሚሴ፣ በደቡብ ወሎ፣ በሰሜን ወሎና በአፋር ክልል የሚገኙ በርካታ አካባቢዎችን ከህወሓት ኃይሎች በማሰለቀቅ መቆጣጠሩን መዘገባችን ይታወሳል።

XS
SM
MD
LG