በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የእርዳታ ተቋማት የተከለከሉ መሳሪያዎችን ወደ ትግራይ እየላኩ ነው ስትል ኢትዮጵያ ከሰሰች


ፎቶ ፋይል፦ መቀሌ
ፎቶ ፋይል፦ መቀሌ

ኢትዮጵያ በጦርነት ወደ ተጎዳው ትግራይ ክልል እርዳታ የሚያደርሱ ተቋማት ታጣቂዎች ሊጠቀሙባቸው የሚችሉ የተከለከሉ መሳሪያዎችንና ከተፈቀድው በላይ ነዳጅ እያደረሱ ነው ስትል በእርዳታ ማጓጓዝ ላይ ጠንከር ያለ ቁጥጥር እንዲደረግ ጠይቃለች።

ለሦስት ወራት ወደ ትግራይ ክልል ሳይደርስ የቆየውና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እግድ ተጥሎበት እንደነበር የሚገልፀው አፋጣኝ እርዳታ ከሚያዚያ ወር ጀምሮ እንዲደርስ የኢትዮጵያ መንግሥት ፈቃድ የሰጠ ቢሆንም፣ የእርዳታ ተቋማት የተከለከሉ መሳሪያዎችን ጨምረው ወደ ትግራይ እየላኩ ነው ሲል ክስ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በሰሜን ምዕራብ የሚገኘውን የአፋር ክልል በጎበኙበት ወቅት ባደረጉት ንግግር "መሳሪያዎች ወደ ህወሓት እንዳይተላለፉ መከላከል ላይ ልዩ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል" ሲሉ ተናግረዋል።

አክለውም አሸባሪ ሲሉ ለጠቀሱት ቡድን አላማ የሚውል፣

"ከተፈቀደው በላይ መጠን ያለው ነዳጅ እና የተከለከሉ መሳሪያዎችን ለማጓጓዝ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስተውያለሁ" በማለት ጉምርክ እና ሌሎች ተቋማት የታገዱ መሳሪያዎች ላይ ቁጥጥር እና ክትትል ለማድረግ የሚያደርጉት ጥረት መጠናከር አለበት ብለዋል።

ሆኖም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እነዚህ የተከለከሉ መሳሪያዎች የትኞቹ እንደሆኑ ለይተው አልገለፁም።

በሌላ በኩል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሬክ ባለፈው ሳምንት ባካሄዱት እለታዊ መግለጫ ተቋሙ ወደ ትግራይ፣ አፋር እና አማራ ክልል ርዳታ ማድረስ መቀጠሉንና ባለፈው ሳምንት ተመጣጣኝ ምግቦችን እና ለቤት ውስጥ የሚያስፈልጉ እቃዎችን የጫኑ 320 የጭነት መኪናዎች በሰመራ አባላ በኩል ወደ ትግራይ መግባታቸውን አስረድተዋል።

ቃል አቀባዩ አክለው ከሚያዚያ ወር አንስቶም የምግብ ርዳታ በ68 የትግራይ ወረዳዎች መሰራጨቱን እና ከ500 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የክልሉ ነዋሪዎች መድረሱን ያመለከቱ ሲሆን የነዳጅ አቅርቦት ዝቅተኛ መሆን ግን የስራ ሂደቱን እያስተጓጎለ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የመንግስታት ድርጅቱ ከመጋቢት አጋማሽ ጀምሮ በአማራ ክልል አንድ ሚሊየን ለሚሆኑ ሰዎች የምግብ ርዳታ እንደተሰጠና ከየካቲት መጨረሻ ጀምሮ ደግሞ በአፋር ክልል ወደ 924 ሺህ ለሚጠጉ ሰዎች ርዳታ መድረሱን ገልጿል።

/ዘገባው የአሶስዬትድ ፕሬስ ነው/

XS
SM
MD
LG