በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ጦርነት እና ድርቅ ኢትዮጵያን ለአስከፊ ሁኔታ ማጋለጡን ምግብ ፕሮግራም አስታወቀ


ፎቶ ፋይል፦ ሰዎች ትግራይ ክልል ውስጥ አጉላ ከተማ አቅራቢያ በማኅበረ ረድዔት ትግራይ የሚታደል ምግብ ለመውሰድ በእግራቸው ሲጓዙ ሚያዝያ 30/2013 ዓ.ም.
ፎቶ ፋይል፦ ሰዎች ትግራይ ክልል ውስጥ አጉላ ከተማ አቅራቢያ በማኅበረ ረድዔት ትግራይ የሚታደል ምግብ ለመውሰድ በእግራቸው ሲጓዙ ሚያዝያ 30/2013 ዓ.ም.

በአፍሪካ ቀንድ የተከሰተው በታሪክ ያልታየ ድርቅ ወደ 20 ሚሊየን የሚጠጋ ሕዝብን ለረሃብ እንደሚያጋልጥ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል። በኢትዮጵያ ብቻ፣ በሰሜኑ አካባቢ የሚካሄደው ጦርነት ታክሎበት ከሰባት ሚሊየን ሕዝብ በላይ በምግብ እጥረት እየተሰቃየ መሆኑንም ተገልጿል።

ለአራት ተከታታይ ወቅቶች ዝናብ ባለመዝነቡ በአፍሪካ ቀንድ እንደ አውሮፓውያን የቀን አቆጣጠር ከ1981 ዓ.ም ወዲህ ያልታየ ድርቅ ተከስቷል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ለአሜሪካ ድምፅ እንደተናገረው፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ግጭት፣ በደቡብ ከተከሰተው ድርቅ ጋር ተዳምሮ፣ ሀገሪቱ ለአስከፊ ሁኔታ እንድትጋለጥ አድርጓል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ቃል አቀባይ የሆኑት ክሌር ኔቪል አስቸኳይ ርምጃ ከተወሰደ፣ እጅግ አስከፊ ሊሆን የሚችለውን ውጤት ማስቀረት የሚቻል መሆኑን ገልፀው “ያ የሚሆን ግን አይመስልም” ይላሉ።

አያይዘው "እንደ አውሮፓውያን የቀን አቆጣጠር ከ2016 እስከ 2017 ድረስ ተከስቶ የነበረው ድርቅ ሊደርስ የነበረውን አስከፊ ሁኔታ ማስቀረት የተቻለው አስቀድሞ ርምጃ በመወሰዱ ነበር።

በ2022 ግን በአቅርቦቶች እጥረት ምክንያት እየከፋ የመጣውን ሁኔታ ሁኔታ ማስቀረት አይቻል ይሆናል የሚል ፍርሃት አለ።" ብለዋል።

በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢ ከሆኑ ድርጅቶች በአንዱ የፖሊሲ አማካሪ የሆኑ እና ስማቸው እንዳይገለፅ የጠየቁ ኃላፊ እንደተናገሩት፣ መንግሥት ሙሉ ትኩረቱ በጦርነቱ እና ለዛ በሚደረግ እንቅስቃሴ ላይ የነበረ በመሆኑ በደቡብ ለተከሰተው ድርቅ በወቅቱ መደረግ የነበረባቸው ዳሰሳዎች እና ምላሾች ሳይደረጉ መቅረታቸውን ተናግረዋል። ይህ ትኩረት ማጣት ደግሞ እጅግ መጠነ ሰፊ የሆነ መተዳዳሪያ፣ ንብረት እና የቀንድ ከብት እንዲጠፋ ማደረጉን አማካሪው ጨምረው ይገልፃሉ።

ዊሊያም ዴቪሰን መቀመጫውን ቤልጂየም ላደረገው ዓለም አቀፍ የግጭቶች አጥኚ ቡድን የኢትዮጵያን ጉዳይ የሚከታተሉ ተንታኝ ናቸው።

"የሰብዓዊ ተኩስ አቁም ቢደረግም ወደ ትግራይ የሚገባው በሳምንት አንድ የጭነት መኪና ነው። ይህ ለሰብዓዊ ርዳታ ሰጪዎች የተፈለገው ያልተገደበ ተደራሽነት አይደለም። የፌዴራል መንግሥቱ ለትግራይ የሚያስፈልጉ እንደ ባንክ፣ ስልክ እና መብራት የመሳሰሉ መሰረታዊ የህዝብ አገልግሎቶችን ለመጀመር ምንም እንቅስቃሴ አለማድረጉም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።" ብለዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ መሰረት በሰሜን ኢትዮጵያ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች፣ በደቡብ በድርቅ በተጠቁ አካባቢዎች ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ተደምሮ፣ በአጠቃላይ ወደ 12.5 ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎች እርዳታ ያስፈልጋቸዋል።

XS
SM
MD
LG