በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ታጣቂዎች ከመዘዞ ፖሊስ ጣቢያ መሣሪያ መዝረፋቸው ተሰማ


ታጣቂዎች ከመዘዞ ፖሊስ ጣቢያ መሣሪያ መዝረፋቸው ተሰማ
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:43 0:00

ታጣቂዎች ከመዘዞ ፖሊስ ጣቢያ መሣሪያ መዝረፋቸው ተሰማ

በአማራ ክልል መዘዞ ከተማ ታጣቂዎች አንድ የፖሊስ ጣቢያን ለተወሰነ ሰዓት ተቆጣጥረው መሣሪያ መውሰዳቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለቪኦኤ አስታውቀዋል።

ክልሉ ውስጥ ሰሞኑን የተስተዋለው በነዋሪዎችና በፌዴራል ሠራዊት መካከል ያለው ግጭት የጀመረው ባለፈው ሳምንት ሲሆን ይህም መንግሥት የክልሎች ልዩ ኃይሎች ፈርሰው ከፌዴራል መከላከያ ኃይሎችና ከፖሊስ ጋር እንዲቀላቀሉ መመሪያ ማስተላለፉን ተከትሎ የመጣ ነው።

በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች ውስጥ የተኩስ ልውውጥ እንደነበረና የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡን ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ትናንት [ረቡዕ] ማለዳ ከበድ ያለ የተኩስ ድምፅ መስማታቸውን፤ ይህም “ፋኖ” እየተባሉ የሚጠሩ የአማራ ታጣቂዎች አንድ የፖሊስ ጣቢያን በተቆጣጠሩበት ወቅት የተፈጠረ እንደነበረ የመዘዞ ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

“ፋኖዎቹ ዒላማ ያደረጉት ለርክክብ የመጣን የጦር መሣሪያ ነበር” ሲል ‘ለደኅንነቴ እሰጋለሁ’ በሚል ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ አንድ ነዋሪ ለቪኦኤ ገልጿል።

“ከሌሊቱ 10 ሰዓት አካባቢ ፖሊስ ጣቢያው ላይ ከባድ ተኩስ ነበር። ጣሪያዎቹ ላይ ጥይት ይዘንብ ነበር። ፖሊሶቹን ስንጠይቃቸው ታጣቂዎች ተኩስ እንደከፈቱባቸው ነገሩን። መጀመሪያ መሣሪያዎቹን በሰላም እንዲሰጧቸው ጠየቋቸውና ከዛ ተኩሱ ተከተለ። ብዙ ነበሩ። ከዚያ ታጣቂዎቹ መሣሪያውን ጭነው ከማለዳው 11 ሠዓት ተኩል አካባቢ ሄዱ።”

እንደ “ፋኖ” ያሉ የክልል ልዩ ኃይሎች ፈርሰው ከፌዴራል ጦርና ፖሊስ ጋር እንዲቀላቀሉ መንግሥት ባለፈው ሣምንት ትዕዛዝ ማውጣቱን ተከትሎ በአማራ ክልል ተቃውሞና ግጭት ተቀስቅሷል።

ክልሉ ውስጥ በተከሰተው ግጭት የተጎዱ ሰዎችን ቁጥር ወዲያውኑ ማወቅ ባይቻልም ማክሰኞ ዕለት በርካታ ሰዎች በጥይት እንደተመቱ የሮይተርስ ዜና ወኪል የኮምቦልቻን ከንቲባ ጠቅሶ ዘግቧል።

“ፌዴራል ሠራዊት የአማራ ልዩ ኃይልን አግቷል” የሚል “የሃሰት” ያሉት ወሬ ከተሠራጨ በኋላ የተቃውሞ ሠልፈኞች አንድ የጦር ሠፈር ማጥቃታቸውን ከንቲባ ሞሃመድ አሚን ለሮይተርስ በሰጡት ቃል ገልፀዋል።

ብዛታቸውን ማረጋገጥ ባይቻልም ከአዲስ አበባ 130 ኪሎሜትር ላይ በምትገኘው ደብረ ብርሃን ከተማ ውስጥ የተጎዱ ሰዎችን ማየታቸውን እማኞች ተናግረዋል።

ከትናንት በስተያ ማክሰኞ ጀምሮ እየተካሄደ ያለ ግጭት እንዳለ ኢሳያስ እንደሚባል የገለፀ አንድ ነዋሪ ለቪኦኤ ተናግሯል።

“የመከላከያ ወታደሮች ከተማዪቱን እንደሚይዙ ቢናግሩም ለተቃውሞ የወጡት ሰዎች ግን የፀጥታ ኃይሎች ወደዚያ እንዲገቡ አይፈልጉም። ፋኖና የከተማው ነዋሪዎች እንደ ዱላና ቆንጨራ የመሰሉና ያገኙትን ይዘው እየጠበቁ ነው። የመከላከያ ኃይሉ ከባድ መሣሪያ የታጠቀ ነው፤ ይህን ይመስላል ውጊያው።”

እንደ ጎንደርና የክልሉ ዋና ከተማ በሆነችው ባህር ዳር ባለሥልጣናቱ እንደተለመደው ኢንተርኔት አቋርጠዋል ሲሉ ነዋሪዎቹ ለቪኦኤ ተናግረዋል።

በአንድ የባህር ዳር ቡና ቤት ውስጥ ሰኞ በደርሰ ፍንዳታ ሁለት ሰዎች ሲሞቱ ብዙዎች ቆስለዋል።

የካቶሊክ እርዳታ አገልግሎት የሚባለው የረድኤት ድርጅት ሁለት ሠራተኞቹ ወደ አዲስ አበባ በመመለስ ላይ ሳሉ ባለፈው ዕሁድ በጥይት ተመትተው እንደተገደሉበት አስታውቋል።

ግድያው በአካባቢው ካለው ተቃውሞ ጋር ግንኙነት ይኖረው እንደሁ ለጊዜው ባይታወቅም ክልሉ ውስጥ እየተበላሸ የመጣው የፀጥታ ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን ታዛቢዎች እየተናገሩ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ “የክልል ኃይሎች ወደ ፌዴራል ኃይሎች መጠቃለል ለዘላቂ ሠላም አስፈላጊ ነው” ይላሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና የፀጥታ ተቋም የቀድሞ ዲሬክተር ዮናስ አዳዬ።

“ዘጠኝ ወይም አስራ አንድ ልዩ ጦሮች ለኢትዮጵያ ለኢኮኖሚዋም፣ ለማኅበራዊ ዕድገቷም፣ ለዘላቂ ፀጥታዋም አይበጅም።”

አማራ ክልል ውስጥ ካለው ተቃውሞና ግጭት ጋር የተያያዙ የተጎጂዎችን ቁጥር በተመለከተ ፌዴራል መንግሥቱ ያወጣው ማረጋገጫ የለም።

ክልል ኃይሎች “ትጥቅ እንደማይፈቱ” ከፌዴራል ኃይሎች ጋር የማዋሃዱ ሥራ ግን “አስፈላጊ ከሆነ በግድም ጭምር እንደሚከናወን” ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ባለፈው ሣምንት ተናግረዋል።

የፌዴራል መንግሥትና የትግራይ ኃይሎች ባለፈው ጥቅምት የሰላም ስምምነት መፈራረማቸውን ተከትሎ ኢትዮጵያ ሁለት ዓመት ከፈጀ ጦርነት ተላቅቃለች።

በጦርነቱ የአማራ ኃይሎች ከፌደራልና ከኤርትራ ኃይሎች ጋር ወግነው ከትግራይ አማፅያን ጋር ተዋግተዋል። በጦርነቱም በመቶ ሺሆች የሚቆጠር ህይወት ጠፍቷል፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ደግሞ ተፈናቅለዋል።

የቪኦኤዋ ማያ ምሥክር ከአዲስ አበባ ያጠናቀረችውን ዘገባ እንግዱ ወልዴ ወደአማርኛ መልሶታል።

XS
SM
MD
LG