በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኢትዮጵያ መንግሥት የትግራይ ክልልን ከሌላው የዓለም ክፍል ጋር እንዲያገናኝ የአውሮፓ ኅብረት ጠየቀ


ፎቶ ፋይል፦ መቀሌ
ፎቶ ፋይል፦ መቀሌ

በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል አንድ ዓመት ለሚሆን ጊዜ የዘለቀው ከፊል የሰብዓዊ እርዳታ እገዳ፣ ወደ አንድ ሚሊየን ለሚጠጉ ለረሃብ የተጋለጡ ሰዎች እንዲደርስ በመጋዘን የተከማቸውን የምግብ እርዳታ በነዳጅ እጥረት ምክንያት ማድረስ እንዳይቻል አድርጎታል ያለው የአውሮፓ ኅብረት የኢትዮጵያ መንግሥት ክልሉን ከሌላው የዓለም ክፍል ጋር እንዲያገናኝ ጠይቋል።

የአውሮፓ ኅብረት የቀውስ አስተባባሪ ኮሚሽነር ጃኔዝ ላናርች ማክሰኞ ዕለት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በቅርቡ ወደ ትግራይ የሚገቡ የእርዳታ ጭነት መኪናዎች ቁጥር መጨመር አዎንታዊ እርምጃ መሆኑን ገልፀው የአውሮፖ ኅብረት በህዝብ ብዛት ከአፍሪካ ሁለተኛ ከሆነችው ሀገር ጋር ያለውን ግንኙነት ወደ ነበረበት ከመመለሱ በፊት ግን "የበለጠ መደረግ አለበት" ብለዋል። በፌዴራል መንግሥቱ እና በትግራይ ኃይሎች መሀከል ለአንድ አመት ከግማሽ ከተካሄደው ግጭት በኋላም በትግራይ የባንክ፣ የኤሌክትሪክ እና የስልክ ግንኙነት እንደተቋረጠ ነው።

ላናርች አክለው የኢትዮጵያ መንግሥት ወደ ትግራይ በሚገባው ነዳጅ እና የገንዘብ መጠን ላይ የጣለውን ገደብ እንዲያነሳ የጠየቁ ሲሆን፣ የትግራይ ኃይሎች የሚገባውን ነዳጅ ለወታደራዊ አገልግሎት ሊጠቀሙበት ይችላሉ የሚለውን ፍራቻ ለማስቀረት መንግሥት 'የመቆጣጠሪያ አሰራሮችን' ሊዘረጋ እንደሚችል ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በክልሉ ዋና ከተማ መቕለ 950 ሺህ ሰዎችን መመገብ የሚያስችል እርዳታ የተከማቸ መሆኑን በዚህ ወር ያስታወቀ ሲሆን በርካታ ነዳጅ የጫኑ መኪናዎች ወደ ክልሉ እንዳይገቡ በመከልከሉ ግን እርዳታውን በትግራይ ወደሚገኙ የተለያዩ ቦታዎች ማከፋፈል አልተቻለም ብሏል።

"የማከማቻ መጋዘኖቹ ሙሉ ናቸው ነገር ግን እርዳታው በከፍተኛ ሁኔታ ወደሚፈለግበት ገጠራማ ቦታዎች መውሰድ አልተቻለም" ያሉት ላናርች በትግራይ በርካታ ሰዎች ከባንክ ገንዘባቸውን ማውጣት ባለመቻላቸው ይህን እርዳታ ተማምነው የሚጠብቁ መሆናቸውን ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ በተነሳው ግጭት የወጡ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ተከትሎ፣ የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ ይሰጥ የነበረውን 88 ሚሊየን ዩሮ (107 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር) ድጋፍ ባለፈው ዓመት መሰረዙ ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አህመድ በዚህ ወር መንግሥት ባለፈው ዓመት አሸባሪ ብሎ ከፈረጃቸው የትግራይ ኃይሎች ጋር የሚካሄደውን ድርድር የሚከታተል ኮሚቴ መዋቀሩን ያስታወቁ ሲሆን ላናርች "ሁለቱም ወገኖች ሥምምነት ላይ መድረስ እንደሚችሉ አምናለሁ በማለት" በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲሆን ጠይቀዋል።

/ዘገባው የአሶሼትድ ፕረስ ነው/

XS
SM
MD
LG